
በዚህ ርዕስ ላይ አስተያየት ለማቅረብ የተነሳሳሁት በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛ፣ የዐድዋ ድል 125ኛ ዐመት ዝክረ በዓል የካቲት 23/2013 ዓ.ም ሲከበር የተስተዋሉት አንዳንድ አካሄዶች ጥያቄዎችን ጫሩብኝ። ሁለተኛ፣ በማግሥቱ ለማለት በሚያስችል ያህል ማርኩስ ሂክስ፣ ኬይል አትወል እና ዳን ኮሊኒ የተባሉ የአሜሪካ ጦር ኃይል መኮንኖች የካቲት 26/2013 ዓ.ም (March 4, 2021)፣ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ “Foreign Affairs” መጽሔት ላይ “የኃያላን መንግሥታት ፉክክር ወደ አፍሪካ እየገባ ነው” በሚል ርዕስ የደረሱትን ጽሑፍ አወጡ። ፍሬ ይዘቱ፡- “21ኛው ክፍለ ዘመን ቢወደድም ቢጠላም አፍሪካን (እንደገና) የመቀራመት እንቅስቃሴ እየጦፈ ያለበት ዘመን ነው፤” የሚል ነው፤ (ለዝርዝሩ፦ “https://www.foreignaffairs.com/articles/africa/2021-03-04/great-power-competition-coming-africa”)
እኛ ኢትዮጵያዊያን ‹ብንወድም ብንጠላም ወደ ዐድዋ ዘመን ተመልሰናል› ብለን ብናነበውም ያው ይሆናል።
በርዕሱ ላይ ቀደም ሲል ጀምሮ በብዙ ተጽፏል። ለምሳሌ ሊ ዌንግራፍ የተባሉት ተመራማሪ አንድ መጽሐፍ በ2008 ዓ.ም ደርሰው ነበር፤ (Lee Wengraf፣ “Extracting Profit: Imperialism, Neoliberalism and the New Scramble for Africa” 2016።) ይሁንና፣ የአሜሪካንን ጦር መኮንኖች አሁን በ2013 ዓ.ም. “አፍሪካን የመቀራመት እንቅስቃሴ እየጦፈ ነው” ያሰኛቸው ምክንያት ምንድን ነው? ኃያላን መንግሥታት አፍሪካን ለመቀራመት የሚያደርጉት ፉክክርና ትብብር መቼ ቆሞ (አበቅቶ) ያውቅና ነው፣ ስለአንደገና ቅርመት የሚናገሩት? በዚህ አፍሪካን “እንደገና” የመቀራመት እንቅስቃሴ በጦፈበት ክ/ዘመን እኛ ኢትዮጵያዊያንስ በምን ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው? ወይንም እንደ 19ኛው ክ/ዘመን አባቶቻችን የ21ኛውን ክ/ዘመን አፍሪካን የመቀራመት እንቅስቃሴ ለመቋቋም እንበቃ ይሆን ወይ?
የቅርመታው ወቅቶች
አፍሪካን የመቀራመት እንቅስቃሴ የጀመረው ተደጋግሞ እንደሚባለው እ.አ.አ. በ1884 እና በ1885 በበርሊን ተደረጎ ከነበረው ጉባዔ በኋላ አይደለም። ቅርምቱ፣ የአውሮፓ ነጋዴዎች የአፍሪካን ወደቦች ከረገጡበት ከ15ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ የሚከናወን ነው። ቅርመታውም፣ በተለያዩ ሁኔታዎችና ወቅቶች በተለያዩ መንገዶች እየተከናወነ የቀጠለ ነው። ስለዚህም፣ በበርሊኑ ጉባዔ ተሳታፊ የነበሩት ቅኝ ገዢዎች በቅርጫው ለመስማማትና የየድርሻቸውን ቅርጫ (ቅኝ ግዛት) ሕጋዊ (formal) ለማድረግ ያካሄዱት ጉባዔ እንጂ፤ የቅርምቱ መጀመሪያ አልነበረም።
Be the first to comment