ኢትዮጵያ እና የምዕራቡ ዓለም ዕቀባ | አንዳርጋቸው አሰግድ

የኢትዮጵያ እና የዕቀባ ጉዳይ በዓለም–ዐቀፍ ደረጃ የተራዘም ውይይት ርዕስ ሆኖ ሲቀርብ የ2013 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። የመጀመሪያው፣ በ1928 (ከዛሬ 85 ዐመት በፊት) “የመንግሥታት ማኅበር (League of Nations)” ይባል ከነበረው የ58 አገራትት ማኅበር ፊት የቀረበው ነው። ሁለተኛው፣ አሜሪካን ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ እየጣለች ያለው ነው። ይሁንና፣ ሁለቱ ዕቀባዎች በዘመን ብቻ ሳይሆን፤ በምክንያትም ሆነ በይዘት ይለያያሉ።

የመጀመሪያው ዕቀባ፣ ኢትዮጵያን በ1928 ዓ.ም በወረረችው ፋሺስት ኢጣሊያ ላይ ዕቀባ እንዲጣል በጄኔቫው የመንግሥታት ማኅበር አማካይነት ተሞከሮ የነበረው ነው። ወይንም፣ በሁለት የወቅቱ የመንግሥታቱ ማኅበር አባል አገራት መካከል በተነሳው ጦርነት ምክንያት ነበር። ፋሺስት ኢጣሊያ የመንግሥታቱን ማኅበር ስምምነት እና የመተዳደሪያ ሕግ (አንቀፅ 10፣ 11፣ 12፣ 15 እና 16) ጥሳ ኢትዮጵያን ወረረች። በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጋዝ ጢስ (በነጉሠ–ነገሥቱ ቃል “የሞት ዝናብ”) አዘነበች። ኢትዮጵያ በወራሪዋ ኢጣሊያን ላይ ዕቀባ እንዲጣል የመንግሥታት ማኅበሩን ጠየቀች። ኢትዮጵያ ዕቀባ እንዲጣል የጠየቀችው፡–

“ጦርነትን በማንኛውም የማኅበሩ አባል በሆነ ወይንም አባል ባልሆነ መንግሥት ላይ በሚጭር ማንኛውም መንግሥት ላይ፣ ማኅበሩ ወዲያውኑ እና በጋራ ዕቀባ ይጥላል”

ይል በነበረው በመንግሥታቱ ማኅበር አንቀፅ 16 ድንጋጌ መሠረት ነበር።

ሁለተኛው፣ የአሜሪካን አስተዳደር አሁን በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ እየጣለ ያለው ዕቀባ ነው። ይኽኛው አንደኛ፣ በሉዓላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የተጣለ ዕቀባ በመሆኑ ከመጀመሪያው ይለያል። ሁለተኛ፣ አሜሪካ ዕቀባዋን የጣለቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት በተወሰነ ውሳኔ መሠረት ሳይሆን፤ በግሏ በመሆኑ ይለያል። ሦስተኛ፣ ዕቀባው የተጣለው በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እና በዕርዳታ አቅርቦት ተቆርቋሪነት ስም ቢሆንም፤ አሜሪካ የዕቅባ እርምጃዋን ለማስደገፈ የሄደችባቸው መንገዶች እና የተጠቀመችባቸው መረጃዎች፣ የሁሉንም ወገን ድርጊትና ማስረጃ ባግባቡ ያልመረመሩና ያላመሳከሩ በመሆናቸው ምክንያት፣ እጅግ ወገንተኛና አድሏዊ ነው። በመጨረሻ ደግሞ ግን፣ የዛሬው ዘመን ዕቀባ የተዳቀለ ወይንም ዘርፈ በዙ ጦርነት (hybrid warfare) የሚባለው አካል ሆኖ፣ በሥራ ላይ የሚውል ጦርነት በመሆኑ በእጅግም ልዩ ነው።

Continue Reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*