እጃቸው ላይ የወደቅኩባት ዕለት – ዘመነ ካሴ (ከባሕርዳር ማረሚያ ቤት)

መንግስት እኔን መከታተል በጀመረ በአስራ አንድ ዓመቱ ተሳክቶለት ይዞ አሰረኝ። ማክሰኞ ዕለት ተሳካላቸው። ውጥናቸው የሰመረው ባሕርዳርን በረገጥኹ በማግስቱ ነው። ወደዚህች ውብ ከተማ የመጣሁት በአንድ መቶ ሃያ ቀኔ (4 ወር) ነበር። ከነበርኩበት ተነስቼ ባሕርዳር ለመድረስ በድምሩ አስራ ሶስት ሰዓት ከአስር ደቂቃ በእግሬ ተጉዣለሁ፤ የተወሰኑ መንገዶችን በባዶ እግሬ ጭምር። ጉዞዬን ስጀምር አንድ ዓላማ ለማሳካት ነበር። አንዲት ስንጥር ጉዳይ (ከተሳካ) በውስጤ ይዣለኹ።

ዓላማዬ፣ ባሕርዳርን እንደመሻገሪያ ተጠቅሜ ጎጃምን ለቆ መሄድ፣ መራቅ ነበር። ይህንን ለመወሰን በቂ የሆኑ ምክንያቶች ነበሩኝ። ወደ በረሃው ወርጄ ባሳለፍኳቸው አራት ወራት “ዘመነን ለመያዝ” በሚል ዱካው ይገኛል ብለው ባሰቡበት ሁሉ ዙሪያ ገባውን ወታደር ሲያሰማሩ እንደነበር አውቃለሁ። እኔን ለመያዝ በተፈጠሩ ግብ ግቦችና ብሩቱ የተኩስ ልውውጦች ገበሬው በቅጡ አርሶ አልዘራም። የጎጃም ምድር ቀልብ ርቆት ነው የከረመው። በተለይ፣ የኔ የትውልድ ስፍራ አካባቢ ያለው ገበሬ አራቱን ወራት አክራሞቱ የሲኦል ነበር። «የአማራን ህዝብ ማህበራዊ እረፍት መንሳት” የሚለው የጠላቶች ዓላማ ምን ያህል አረመኔያዊ እንደሆነ ለመረዳት አጋጣሚውን አስታክከው በዚህች አጭር ጊዜ በህዝባችን ላይ የፈፀሙት ግፍ ከበቂ በላይ ማሳያ ነበር። ሰዎቹ፣ የጥይት አረራቸውን ጩኸት ፈርቶ በነፍሴ አውጪኝ ሩጫ የሸሸውን ቤቱ ድረስ ተከታትለው በመግባት ከተሸሸገበት አውጥተው በጥይት ከመግደል አልተመለሱም። አቅሟ የከዳት የመነኩሴ እናቴን ደሳሳ ጎጆ ጣሪያ በጥይት እየበሳሱ ሲሳለቁ እጆቿን ወደ ድንግል ማርያም ልጅ ዘርግታ ኤሎሄ ከማለት በቀር እድል አልነበራትም። እንደ ወንበዴ የዘረፉትን ዘርፈው፣ የተረፋቸውን አውድመው ከአንዱ ጎጆ ወደሌላ ሲሸጋገሩ ሰነበቱ። የህዝቡን ነፍስያ ሲያስጨንቁ ከረሙ።

በጥቅሉ፣ ከግንቦት 12 ጀምሮ በአካባቢው ላይ በተፈጸመው ወረራ መሳሪያ ሲያዩ “መጡብኝ” እያሉ የሚጮኹ ህጻናትን ማየት የተለመደ ነበር። ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም፣ መሳሪያ አንጋች መለዮ ለባሾች በሯን ቆርቁረው የምንበላው አምጪ ብለው ያስደነገጧት እናት በድንጋጤ ራሷን እንደሳተች አሁንም አልነቃችም። አራት ልጆቿን ጥላ ራሷን ስታ ወድቃ እንደቀረች ነው። የጥይት ጩኸት ሲሰሙ እየደነበሩ ወደአገኙት የሚሮጡ ከብቶችን መመልከት ዕለታዊ ትእይንት ነበር። ሰውም ከብቱም በአራት ወራት ውስጥ የቁም ስቅሉን ሲያይ ከርሟል። ይህንን መታዘብ እንኳን አይን ነፍስ
ታነባለች።

Continue Reading

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*