
እጅጋየሁ ሽባባው ለትውልዴ ዋስ ናት። ልዩ ናት። አክብሮቴ፤ በቦረቅሽባቸው የቻግኒ ሜዳዎች ቀዝፎ፤ ደጅ በጠናሽባቸው የሸገር ከያኒያን ደጅ አልፎ፤ ሳያውቁ ከገፉሽ የኒውዮርክ ህንጻዎች እየተላተመ ካለሽበት ይድረስሽ። አድዋን በከፍታ ገልጸሽዋል፤ አባይን በደማቁ ስለሽዋል፤ ኢትዮጵያን በምልአት ተርከሻል። አድዋ ብለው አባይን መድገም፤ ሁለቱን ጠርተው ኢትዮጵያን መሰለስ፤ የወግ አዋቂዎች አመል ነው። “አድዋ ዛሬ ናት፤ አድዋ ትላንት” በሚለው ገለጻሽ ከሃያል ተቃርኖ እላተማለሁ። “አባይ ወንዛ ወንዙ፤ ብዙ ነው መዘዙ”ም እያሳሳቀ የሚዋጥ መራር ሃቄ ነው። “ሰላም ይስጡንና አርሰን እናብላቸው” ስትይኝ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስንት ሰው እንደሚያውቅሽ እጠራጠራለሁ። አንዳንዴ ሃሳቦቹን ሶስት ብዬ መቁጠር ይብደኛል። አንድ ይሆኑብኛልና። አንድ ቢሆኑም እንደሶስት ተርከን እንደ አንድ እንደምድማቸው፤ አድዋ ተራራ ነበር፤ ዛሬ ወንዝ ይሆናል፤ ትላንትም እንደዚያው። ወንዝ ያለ ተራራ ህይወት የለውም የሚለው ደግሞ፤ ዝናቡን የሚያወርደው ከተራሮቹ የተሳሳመው ሰማይ ነው። አባይን ሊማርኩ መጡ፣ ወደ አድዋ ወሰዳቸው፣ አድዋ ላይ ሆኖ ኢትዮጵያን ማየት ግድ ነውና ይኸው እዚህ ደርሰናል!!! አድዋ …አባይ ….፤ ኢትዮጵያ!!
ከአባይ ወደ አድዋ፤
1869 ግብጽ፤ ስዊዝ ካናል የሚባለውን አቋራጭ የባህር መስመር ስትታጠቅ፤ አውሮፓውያን ዘንድ ነውጥ ሆነ። ፈርኦኖቹ ድራማዊ በሆነ መልኩ የስትራቴጂካዊ ግብግቡ ማእከል ሆኑ። ነዳጅ እንደውሃ ለሚጠማቸው የአውሮፓ መርከቦች ግማሽ ያህል ጉዞ የሚቀንሰውን ቅርብ መንገድ መያዝ የግቦች ሁሉ ግብ ሆነ። ስለዚህም ከግብጽ ጋር በጋብቻም፤ በሽርክናም፤ በሴራም ሆነ በስራ መዛመዱ አሊያም በጉልበት ማስገበሩ ቀዳሚ ስራ ነበር። ብሪታኒያ ዋና ከተማዋን በቅርቡ ነበር ወደ ካይሮ ያዞረችው። ስለዚህ ካናሉን ፈረንሳይ ብትሰራውም፤ የማይናቅ ሼር ይዛ ባሉካ ባሉካ ብትጫዎትም፤ በእዳና በወለድ ተብትበው በጣሉት ንጉስ ምትክ እንግሊዞቹ ቤተመንግስት ገብተው ነበርና የያዙት ዱላ የማይመጣጠን አይነት ሆነ። የለንደን ሃይለኛ ነበር።
Be the first to comment