“ኦነግ ሸኔ” ማነው?

‹‹…እዚህ ያላችሁት ኦነግ (ABO) ናችሁ። ለማ ኦነግ ነው። ዶ/ር ዐቢይ ኦነግ ነው። ኦነግ ያልሆነ ሰው የለም፣ ወደፊትም አይኖርም። [ከተሰብሳቢው ጭብጨባ…] የራሳችንን ድርጅት የሚጠላ የለም። ኦነግን የሚጠላ የለም። ኦነግ የትግላችን ምልክት በመሆኑ እዚህ ያላችሁ ቄሮዎች እንኮራበታለን ብላችሁ፣ ታግላችሁ፣ ሀገራችንን ነፃ አውጥተታችሁናልና ክብርና ምስጋና ይሁንላችሁ። [ጭብጨባ]..

እዚህጋ መለየት ያለብን ግን፣ ኦነግን ብድግ አድርገን ለሌላ ሰው ከሰጠን እርሱ ትክክል አይደለም። ኦነግ ኦሮሞ ነው፤ ኦነግ እኔ ነኝ፤ ኦነግ አንተ(ች) ነህ (ሽ)። እየተጣላ ያለው ኦነግ እና ኦዴፓ (ODP) አይደለም። ስህተት ውስጥ መግባት የለብንም። ኦነግ ማለት ትግል ነው፣ የትግል ምልክት ነው።…››

ይህ ንግግር የተሰማው ጉምቱ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በተገኙበት የስብሰባ አዳራሽ ሲሆን፤ ጊዜው በለውጡ ማግስት ከሁለት ዓመት በፊት ነው። ተናጋሪው ‹‹የተባበሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር›› የተሰኘው ፓርቲ አመራር የሆኑት ብ/ጀኔራል ኃይሉ ጎንፋ ናቸው። እኒህ ሰው ከዚህ ስብሰባ ጥቂት ወራት በኋላ የወያኔውን ሜ/ጀኔራል ገ/እግዚአብሔር መብራቱን በመተካት የአፍሪካ ሕብረት (AU) የሴኪዩሪቲ ኃላፊ ሆነው መሾማቸው ይታወቃል።

ናይጀሪያዊው የሥነ ጽሑፍ የኖቤል ሎሬት ፕሮፌሰር ዎሌ ሶይንካ ቦኮሐራም የተሰኘው ጽንፈኛ ቡድን እንዴት በሰሜን ናይጀሪያ ፖለቲከኞች እንደተፈጠረና ተኮትኩቶ እንዳደገ ይገልጻሉ። እንደ ፕሮፌሰር ሶይንካ ገለጻ የሰሜን ናይጀሪያ (ሐውሳ ፉላኒ) ፖለቲከኞች “እኛ የማንጠይቃቸውን ጥያቄዎች ይጠይቅልናል፤ እኛ በፖለቲካው ውስጥ የምንሳተፈው የማንሠራቸውን ጽንፈኛ ተግባራት ይፈጽምልናል” ወዘተ. ብለው ኮትኩተው ያሳደጉት ቦኮሐራም የማታ ማታ ለፈጣሪዎቹም የሚመለስ አልሆነም። በሚፈለገው ደረጃ አክራሪ አልሆናችሁም፣ ለዘብተኛ በመሆናችሁ ለሕዝባችንና ለሃይማኖታችን ጠንቅ ናችሁ እየተባሉ ብዙ ፖለቲከኞች ተገድለዋል። ዛሬ ቦኮሐራም ከሕፃናት እስከ አዛውንት፣ ከመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ እስከ ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ከጋዜጠኛ እስከ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን የሚጨፈጭፍ ክንዱ የፈረጠመና ግንኙነቱም ውስብስብ ገጽታ የተላበሰ ድርጅት ሆኗል።

አንድን ዓላማ በኃይል ለማሳካት በመሣሪያነት የሚፈጠሩና የሚደገፉ ድርጅቶች የራሳቸውን ህልውና ዘርተው የፈጠራቸው ባላንጣ እንደሚሆኑ ቦኮሐራም ብቻ ሳይሆን ሶቬት ሕብረትን ለማዳከም በአሜሪካ ሲደገፉ የነበሩት ሙጃህዲኖች ተመልሰው የታሊባንና የአልቃኢዳ መፈልፈያ ጓዳ ሆነው የአሜሪካ ቀንደኛ ጠላት እንደሆኑ ማየት ይቻላል።

Continue reading

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*