ከመቀሌ በኋላ ኢትዮጵያ ወዴት? | በያሬድ ጥበቡ

ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቅቆ ከወጣ እነሆ ወደ ሦስተኛ ሳምንት እየተቃረብን ነው። ይህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ “ፖለቲካዊ” የተባለ ውሳኔ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ዐቀፍ የፖለቲካ ሰዎችንና ተቋማትን ትኩረት በእጅጉ ስቧል። በእርግጥ ምንም እንኳ፣ ‘ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው’ ቢባልም- ቅሉ፤ እኔን ጨምሮ፣ የተወሰኑ ሰዎች ‘ከወታደራዊ ሽንፈት የመነጨ ነው’ የሚል ሙግት መግጠማችን ይታወቃል። ይህ ፍፃሜ በራሱ አንድ ክስተት ብቻ ባለመሆኑና ከተከታይ ተፅዕኖዎቹ አኳያም፣ ‘ከመቀሌ በኋላስ ወዴት?’ የሚል ጥያቄ በብዙ ኢትዮጵያውያን አእምሮ እንዲመላለስ አድርጓል።

ብዙዎች፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምክንያቶች ተቀብለው፣ ‘ውሳኔው ወታደራዊ ሳይሆን፣ ፖለቲካዊ ነው’ ቢሉም፤ እዚያው በዚያው ትግራይን የመክበብ፣ ትግራይን በጨለማ የማኖር፣ ትግራይን የማስራብ፣ ትግራይን ወደ ድንጋይ ዘመን የመመለስ ፍላጎቶችን ሲያንፀባርቁ ይስተዋላሉ። ፖለቲካዊ ውሳኔ ከሆነ፣ ታዲያ እንዲህ ዐይነት የክፋት አስተሳሰቦች ምንጫቸው ምን ይሆን?’ ብሎ ለመጠየቅ እንገደዳለን። በእኔ ግምት፣ “ዱቄት አድርገን በትነነዋል” የተባለው ኃይል ከኢምንትነት ተነስቶ፣ በአጭር ወራት ዐቅም ገንብቶ ያደረሰው ወታደራዊ ሽንፈት በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን፣ አለማመንን፣ ብሽቀትን፣ መከዳትን፣ ጥላቻና ፍርሃትን ፈጥሯል። ከፍርሃቱም አንዱ ‘ወያኔ ከመቀሌ በኋላ ወዴት ልትሄድ ነው? አዲስ አበባ ድረስ ትመጣ ይሆን?’ የሚለው ይመስለኛል።

ባለፉት ሦስት ዐመታት በነበረው የዐቢይ አስተዳደር ከሥርዐቱ ጋር የተነካካው፣ አገሩን ወደ ዴሞክራሲያዊ ተስፋ ያሸጋገረ መስሎት የደከመው… ሰው ብዙ ነው። በዐቢይ ዘመን የተንሰራፉትን መጠነ-ሰፊ ግድያዎች፣ መፈናቀሎችና አለመረጋጋቶች የሚፈቱት በምርጫ ነው በሚልም፣ ሙሉ ትኩረታቸውን ምርጫው ላይ አድርገው ተስፋቸውን የጣሉ ዜጎች ጥቂት አልነበሩም። የምርጫው ውጤት ገና እየተቆጠረ፣ መከላከያው ከትግራይ በመውጣቱ የሰነቁት ተስፋ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ቸለሰበት እንጂ። የምርጫው ሂደትም፣ በ97.4% ውጤት ሲጠናቀቅ፣ ምርጫው አገርን ከችግር እንደማይታደግ ግልፅ ሆነ። ምናልባት ከዚህም በተነሳ፣ ትላልቅ ምሁራን ሳይቀሩ፣ የትግራይ ወገኖቻችንን እየጠረዙ ወደ ትግራይ መመለስን፣ እንደአማራጭ ሃሳብ ሲያቀርቡ፤ መንግሥት ደግሞ ቱሉ-ዲምቱን በመሳሰሉ ቦታዎች በፈጠራቸው ማጎሪያዎች ከትግራይ ወደ መሃል አገር የሚመጡትን ማሰር ሙያዬ ብሎ ይዞታል። ከዚህም አልፎ፣ በ22 ማዞሪያና በሌሎች የአዲስ አበባ ቀበሌዎች የሚኖሩትን ከሕግ ውጪ እያሰረና የንግድ ተቋሞቻቸውን እየዘጋ መሆኑ ተዘግቧል። እነዚህ እርምጃዎች የትግራይ አማፂያንን ግስጋሴ ያፋጥኑታል እንጂ፣ ወደ መፍትሄ አያቀርቡም። ይህም፣ ወደ አጠቃላይ አገራዊ ቀውስ ሊመራ ይችላል። ለምን እንዲህ እንደምል በዝርዝር ላስረዳ።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*