ከድጡ ወደ ማጡ | በፍቃዱ ኃይሉ

አንዳንድ ዐመታት በታሪክ ይታጨቃሉ፤ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስድስት ዐመታት ይልቅ፤ የዶ/ር ዐቢይ አህመድ አራት ዐመታት በብዙ እጥፍ ይረዝማል። ዐቢይ በአራት ዐመታት ቆይታቸው፣ የኢትዮጵያ መሪዎች እየተፈራረቁ ያዩትን የሚያኮራ ቅፅበት፣ የሚያሳፍር ክስተት በሙሉ አይተዋል ማለት ማጋነን አይሆንም። በአጭር የሥልጣን ዘመናቸው፣ ሕዝባዊ የደስታ ፈንጠዝያ እና የሐዘን ሙሾ እንደ ጉድ ተርከፍክፏል። እርሳቸውም እንደ መልዓክ ተወድሰዋል፤ እንደ ሰይጣን ተረግመዋል። የታሪክ ድርሳናት ውስጥ አንድ ምዕራፍ መሆናቸው ካሁኑ ታውቋል፡፡ “እንዴት ይታወሱ ይሆን?” የሚለውን ለመተንበይ ጊዜው ገና ነው። አሁን የሚቻለው አካሔዳቸውን መገምገም ነውና፤ በዚህ መጣጥፍ የአራት ዐመት የሥራ ዘመናቸውን እንደሚከተለው እገመግማለሁ።

በዚህ ጽሑፍ “ዐቢይ አህመድ በዝግታ ፈንቅለውት ከቀየሩት የቀድሞ ፓርቲያቸው ባህርያት፡- የቱን አስቀጥለዋል? የቱንስ ከባርኔጣቸው ጋር ቀይረውታል? አጭርም ቢሆን፣ ዘመነ መንግሥታቸው ሕዝቦች ከታገሉት የኢሕአዴግ አገዛዝ ተሽሏል ወይስ ከፍቷል?” ብለን እየጠየቅን እንመልሳለን።

ከአመራር ወደ መሪ
“Abiy is the Party!”

ኢሕአዴግ በዐቢይ መግነን ዋዜማ ራሱን ሲገመግም “ሕዝበኝነት” (populism) ‹ፓርቲዬ ውስጥ አቆጥቁጧል› ብሎ ነበር። ያለምንም ጥርጥር የዚያ ሕዝበኝነት ኮከብ ሆነው የወጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩ ነገሮች በተከሰቱ ቁጥር የምሥራቹን ይዘው ወይ በቴሌቪዥን መስኮት፤ አልያም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ብቅ ይላሉ። ጥፋቶች ሲኖሩ ደግሞ፣ ተሰውረው ሰንብተው ሐዘኑ ሲረግብ ብቅ ይሉና፣ ሌሎችን ይወቅሳሉ። በዚህ መንገድ ብዙሃኑ እርሳቸውን ከየምሥራቹ ጋር ብቻ አገናኝተው እንዲያስታውሷቸው ጥረዋል፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን ያድርግ?” ይላሉ ወዳጆቻቸው።

ኢሕአዴግ በሥልጣን ሽኩቻ ተሰንጥቆ፣ ሕወሓት የሌለበት ብልፅግና ሲወለድ፣ የማይነቀነቅ የሥልጣን ብቸኛ ባለቤት ሆነው ወጥተዋል። በአቦይ ስብሓት ነጋ ቋንቋ “ኢሕአዴግ ውስጥ አመራር እንጂ፣ መሪ የሚል ነገር አልነበረም፡፡” ምክንያቱም ውሳኔ የሚሰጡት ‹ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት› በሚሉት መንገድ በውስጥ ለውስጥ የፖለቲካ ስምምነት ነበር። እንዲያም ሆኖ፣ መለስ ዜናዊ የማይነቀነቅ ሥልጣን ጨብጠው ነበር።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*