ከጦርነቱ በኋላ የሚመጣውን ስለማሰብ… | ጌታቸው ሽፈራው

አሸባሪው ትሕነግ ጦርነቱን ሕዝባዊ ቅርጽ ሰጥቶ የዐማራ ክልል አካባቢዎችን ከወረረ ሦስተኛ ወሩን ተሻግሯል። ከሰኔ መጨረሻ ጀምሮ እያካሄደ ባለው ወረራም በርካታ የጦር ወንጀሎችን ፈጽሟል። ተጽእኗቸው ገናና ለሆነው የምዕራብ አገራትም ‹ፍፁማዊ ተላላኪ› በመሆኑም፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ረገድ በዓለም ዐቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚያስጠይቁ ድርጊቶችን ደጋግሞ ቢፈጽምም፤ ግሳፄ እንኳ ሳይደርስበት በወረራው ቀጥሏል።

የኤርትራውያን መከራ በትግራይ

በዓለም ዐቀፍ ሕግ ልዩ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ስደተኞች ሳይቀር፣ የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል። “ሽመልባ” እና “ህጻጽ” በሚባሉ መጠለያ ጣቢያዎች በነበሩ የኤርትራ ስደተኞች ላይ በፈጸመው ጥቃት ከሦስት መቶ በላይ ስደተኞች ህይወታቸው ቢያልፍም፤ ዓለም ዐቀፉ ማኀበረሰብ “ጉዳዩ አሳስቦኛል” ከሚል ዘወትራዊ ማሳሰቢያ ባለፈ፣ የወሰደው እርምጃ የለም። በጥቃቱ ሁለቱም መጠለያዎች አገልግሎት መስጠታቸው ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ፣ ስደተኞቹ ወደተለያዩ አካባቢዎች ተበትነዋል። ትሕነግ ትግራይን መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ፣ በክልሉ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎች የነበሩ ወደ 24,000 የሚጠጉ ኤርትራውያን ሰብዓዊ ድጋፍ እንደተቋረጠባቸው ‹የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን› ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ ያሳወቀ ቢሆንም፤ ባለፉት ሁለት ወራት ቡድኑ ላይ ይህ ነው የሚባል ጫና አልተፈጠረም። ከዚህ ይልቅ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወንጀል ተጠምዶ ታይቷል። የተራድኦ ድርጅቶችን ካሚዮን ተሸከርካሪዎች ጨምሮ፤ ልዩ ልዩ መሠረተ ልማቶችን ለወታደራዊ አገልግሎት እያዋለ የሚገኘው ትሕነግ፣ የዓለም ዐቀፉ ማኀበረሰብ ዝምታ በምዕራባውያኑ ባርኮት ኢትዮጵያን እንዲያፈርስ ተልዕኮ የተሰጠው አስመስሎታል። ከጥቅምት 24/2013 በፊት በትግራይ ከ100 ሺሕ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። እነዚህ ስደተኞች አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ዓለም የሚያውቀው ነገር የለም።

መረጃዎች እንሚያመለክቱት ትሕነግ፣ በትግራይ ይገኙ ከነበሩ ኤርትራዊያን ስደተኞች ውስጥ ወንዶችን ለይቶ በብዛት ረሽኗል። በማይካድራ ከ1,600 በላይ የዐማራ ተወላጆች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የፈጸመው ‹ሳምሪ› የሚባለው የትግራዩ ‹ኢንተር ሃይሞይ›፣ ኤርትራውያን በተጠለሉበት የስደተኞች ጣቢያ በመግባት ዓይናቸውን በስለት እያወጣ ጭምር፣ ስለመግደሉ መረጃዎች ሾልከዋል። ዋናው ጭፍጨፋ የተፈጸመው በ1996 ዓ.ም በተመሰረተ የሽመልባ ስደተኛ ጣቢያ ሲሆን፤ ከኢትዮ- ኤርትራ ድንበር በቅርብ ርቀት እንደሚገኝ ልብ ይሏል።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*