
በዚህ ዐውድም ባለፈው የጀመርነውን የዓይን ምስክሮች ቃል ማስነበብ እንቀጥላለን። ለግለሰቡ ትዝብትም ብእሬን አውሰዋለሁ።
…ከወልዲያ ቀጥሎ ለብዙ ቀናት የከረምኩት ሮቢት ከተማ ነው። በከተማዋ ግራ-ቀኙን የሚወጣ የሚወርደው ሕዝብ ብዙው የደጋ አርሶ ዐደር ነው። የቆላው አርሶ ዐደር ራሱን በጎበዝ አለቃ አደራጅቶ ውጊያ ከገባ ቆይቷል። በደኅናው ጊዜ በሚያዚያ እና በሰኔ ወር የተዘራው ሰብል፣ በአብዛኛው በአረም ከመዋጡ በዘለለ (በተለይ ጥሬ-ነክ ሰብል)፤ በአውሬ እና እረኛ ባጡ የቤት እንስሳት መበላቱን ሰምቻለሁ።
ቆቦ በተወረረ ሰሞን በሽብር ወሬ ተዋክበው የሸሹ አርሶ ዐደሮች ተመልሰው የተበተኑ ከብቶቻቸውን ለመሰብሰብ ከመቸገራቸው ጋር ተያይዞ የአውሬ ሲሳይ ሆነዋል። ብቻ በእንዲህ ዐይነት የጥፋት ዜና እየቆዘምሁ ሮቢት ስከርም፣ የገበያዋን ሁኔታ በጨረፍታ ታዝቤለሁ።
‹‹ሮቢት ገበያ አልቀርም የግድ፣
የምይዘው ባጣ ተሸክሜ ግንድ፤›› በሚለው ስንኝ ውስጥ የተሸሸገውን ማኅብረሰባዊ ትርክት ሳስተረጎመው፣ እንዲህ የሚል አንድምታ አገኘሁ፡- ሮቢት (ረቡዕ ገበያ) በሳምንት አንዴ ከተጠባቂነቱ በተጨማሪ፤ ከ20 በላይ የሚገመቱ ቀበሌዎች የሳምንት ቀለብ የሚያዘጋጁት በዚህ ዕለት ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው። በዕለቱ መገበያያ ገንዘብ ያጣ የገጠር ሰው (በርግጥ፣ በአሁኑ ወቅት ደኑ ተመናምኗል) እንጨትም ቢሆን ሽጦ የቤት ጣጣውን የመሙላት አማራጭ ነበረው።
ወትሮም ገበያ የድሃ እና የሀብታም መገናኛ ነው። ያጣው ባገኘው ተጣጥቶ የዕለት እንጀራውን ቀምሶ ያድራል። ዛሬ ግን፣ የነበረው እንዳልነበረ ሆኗል። ምክንያቱም ሕዝብ ገበያ ወጥቶ በተመሳሳይ የችግር ደዌ ተፋጧል። የሚሸጡት ቢኖር፣ የሚገዙበት ገንዘብ ከባንክ ማውጣት አልቻሉም። የሚያስፈጩት እህል ቢኖር፣ መብራት ስለተቋረጠ እንደ ድንጋይ ዘመን በባሕላዊ ወፍጮ ለመገልገል ሲገደዱ አይቻለሁ።
Be the first to comment