
ፈር መያዣ
የታሪክ ፕሮፌሰሩ ሽፈራው በቀለ፣ የፖለቲካ ፕሮፌሽን ግርማ-ሞገስና አክብሮት የሚጎናጸፍበት ዐውድ በቀጥታ ከሌጂትሜሲ (ቅቡልነት) ጋር እንደሚቆራኝ ከገለጹ በኋላ፡- “አብዮት ካመጣቸው ብዙ መዘዞች አንዱ፣ የፖለቲካ ፕሮፌሽናል ደረጃ እየወደቀ መሄድ ነው። ‹ፖለቲካ› ማለት መቀላመድ፣ የመንግሥትን እና የአገርን ሀብት ልፎ ለልጅ ለልጅ ልጅ፣ ለዘመድ አዝማድ፣ ለአምቻ ጋብቻ፣ ለዝርያ ለጎሳ ‹ጮማ መቁረጥ ጠጅ ማፍሰሰ› ማለት ሆኗል። በኢትዮጵያዊያን አእምሮ ውስጥ በፖለቲካ እና በማፊያ መካከል ልዩነቱ እየደበዘዘ ሄዷል ማለት ይቻላል። […] ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች የተከበሩ ካልሆኑ፣ ጨዋ የጨዋ ጨዋ ካልሆኑ፣ ለአገር አሳቢ፣ ለወገን ተቆርቋሪ ካልሆኑ፣ የሚናገሩት መሬት ጠብ የማይል ካልሆኑ፣ ምንም ያህል ውብ ውብ ርዕዮችን ስንደቀድቅ ብንውል፣ ርዕዮቻችን ዋጋ አይኖራቸውም፤” ሲል ያስረግጣሉ።
ፕሮፌሰር ሽፈራው ይህንን ያሉት “አብዮት፣ ሌጂትሜሲና ፖለቲካ፡- ሦስት አበይት ሒደቶችና ርዕይ 2020” በሚለው የ1996ቱ የፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ጽሑፍ ላይ በሰጡት አስተያየት ነው።
ፕሮፌሰር ሽፈራው ይህንን ግምገማቸውን በጽሑፍ ካቀረቡ ከ18 ዐመት በኋላ ያለውን የአገራችንን የፖለቲካ የሞያ ደረጃ ስንመለከተው፣ ከነበረበትም የበለጠ ማሽቆልቆሉን እንረዳለን። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ያሉት መሪዎች የሚናገሩትና የሚሠሩት የማይገናኝ በመሆኑ፣ በሕዝብ እና መንግሥት መሃል ያለው ግንኙነትና ትምምን (trust) በእጅጉ ተበላሽቷል። የፖለቲካ መሪዎች የሚናገሯቸውና የሚገቧቸው ቃሎች የማይጨበጡና የማይታመኑ እየሆኑ፣ ሕዝቡ በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ያለው ትምምን ለዜሮ የቀረበ ሆኗል። “ሳናጣራ አናስርም” ተብሎ፣ በተግባር የሆነው ሲታይ፤ “ሕወሓት የተበተነ ዱቄት ነው” ተብሎ፣ በኋላ የተፈጠረው ሲረጋገጥ… ሕዝቡ የመሪዎቹን ቃል አላምንም ቢል አይፈረድበትም። የብልፅግና መሪዎች ቃልና ተግባር የሰማይና የመሬት ያህል እየተራራቀ፣ አገሪቱም ወደ ግጭት መናኸሪያና የተፈናቃይ መጠለያ ማዕከልነት እየተቀየረች መጥታለች። ይህም ብዙዎችን ከሰላምና መረጋጋት አንጻር ‹ያለፈው አገዛዝ ይሻለን ነበር› ወደሚሉበት ጠርዝ እየገፋቸው ነው።
አምባገነንን መናፈቅ?
በአገራችን በየአካባቢው የሚታየው የማያቋርጥ ብሔር-ተኮር ግጭት እና የገባንበት እጅግ አውዳሚ የእርስ-በርስ ጦርነት፣ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ‹ከዴሞክራሲ ይልቅ፣ ሕግና ሥርዐትን አስፍኖ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የሚጠበቅ አገዛዝ ይሻላል› የሚል ስሜት የፈጠረ ይመስላል። ደፈር ብለው ‹የኢሕአዴግ አገዛዝ የተሻለ ነበር› የሚሉ ወገኖችም አልታጡም። በርግጥ፣ ሕዝባችን ከገባበት አረንቋ አኳያ፣ ያለፈውን ግፈኛ አገዛዝ ቢናፍቅና አምባገነንነትን ቢመኝ የሚገርም አይደለም። ከሁሉም በፊት በህይወት መኖርና በሰላም ወጥቶ መግባት ይቀድማልና።
Be the first to comment