ዐቢቺኒያ-፪ | በዋጋዬ ለገሰ

“ለጄኔራሎቹ የመፈንቅለ መንግሥትን ነገር ፈጽሞ እንዳይሞክሩት አሳስበናቸው ነበር። በሃሳባቸው እንደሌለ ነበር የነገሩን። ከፕሌን ስንወርድ መፈንቅለ መንግሥቱ መፈጸሙን ሰማን!” ይላል የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልእክተኛቸው የነበረው ፌልትማን።

“ይሄ፣ የአሜሪካ ጉልበት ምን ያህል እንደተዳከመ አንዱ ማሳያ ነው፤” ይላሉ የብሩኪንግስ ተንታኞቻቸው። የሱዳን ጄኔራሎች፣ አንጋፋውን ዲፕሎማት ሙድ ይዘውበታል። ለእነ ሳማንታ ፓወርም ተመሳሳይ ነበር። የእነ ፌልትማን ታሪክ በዚህ አያበቃም። ለተፈንቃዩ ጠቅላይ ሚኒስትርም “የዚያን ጄኔራል የወርቅ ኮንትሮባንድ ቶሎ በጣጥስልን?!” ብለዋቸው ነበር። ባለ ወርቁ ንግግራቸውን ከቢሮው ቁጭ ብሎ እያደመጠ ነበር። የአሜሪካውን ዲፕሎማት ምስጢራዊ ሰብሰባ፤ ጠልፎ የሚሰማ የሱዳን ጄኔራል ከወደ ቻድ ብቅ ብሏል። እድሜ ለቴክኖሎጂ!!

“ግመል ነጋዴውን ጄኔራል በሰርቪላንስ-ቴክ እንዲህ ያራቀቁት ቻይናዎቹ ናቸው” ይላሉ የካቶ ሴንተሮቹ ተንታኞች። “ድፍን ምስራቅ አፍሪካን እንዲህ ያደረጉብን፣ ያጠገቡብን እነሱ ናቸው፤” ሲሉም ያክላሉ።

እነ ፌልትማን ከቻይና የሚብስ ጉዳይ የላቸውም። ካርቱም ድረስ ወርደውም፤ ሸገር ወጥተውም አጀንዳቸው ቻይና ናት። ከሞቃዲሹ አስመራ፣ ከካምፓላ እስከ ጅቡቲ ቻይናን ያሳድዳሉ። የአደን ፋራህ ሹመት፣ የቢቂላ ሁሪሳ ቃለ መጠይቅ ያሳስባቸዋል። የማኦ መንፈስ ከምንጩ ይደርቅ ዘንድ በርብርብ ይፋለሙታል። የቻሉበት አይመስልም። በሚያገኙት ምላሽ ደንግጠው ሲያበቁ ይገረማሉ። ምደረ ዲክታተር በኮንፊሺየስ ወግ ተራቅቆላቸዋል። በቻይና ሞዴል ጋሻውን አሰርቶ፣ ያዝጋቸዋል። የአሽከሮቻቸው መቀለጃ የሆኑ ይመስላል። ሁለት ሦስቴ ተመላልሶ ማስቦካካትን “ዲፕሎማሲ” ይሉታል። በታሪክ ሆኖ በማያውቅ መልኩ፣ የአፍሪካ ቀንድ ትግል ገጠማቸው። በእነሱ እርዳታ ውሎ እያደረ፣ ‹በቻይና ጉዳይ አልደራደርም› ይላቸዋል። ሕወሓትን ከሞት መቀስቀሱ፣ ሻዕቢያን ለመፈንቀል ማሰቡ፣ አልሸባብን ማጋጋሉ፣ ብልጽግናን መወጠሩ… ወዘተ የፀረ ቻይናው ትግል ዋና አካል ነው። ለምን? እንዴት?

በአፍሪካ ቀንድ ሰሞኑን

ቻይና በታሪኳ የመጀመሪያውን ሹመት ሰጥታለች። ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ መድባለች። “ቀጣናዊ አንድነት፣ ኢኮኖሚያዊ ጥምረት፣ የቀጣናውን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል፤” የሚል ዐይነት ሃሳብ ይዘውም በየአገራቱ ዞረዋል። ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ ኬኒያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ በደማቁ ተቀብለዋቸዋል። “አገራቱምን በኢኮኖሚ ማስተሳሰር ለዘመናት በቀጣናው የራቀውን ሰላም ያመጣል፤” ባይ ናቸው። ያው ይሄ ሃሳብ አሜሪካንን ሊያስደስት አይችልም። ሕወሓት “የኢሳያስ አጉል ቅዥት” ሲል የሚያጣጥለው ይሄንን ነው።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*