ዘመቻ ደምድም | ተመስገን ደሳለኝ

ዛሬ፣ ኢትዮጵያ የቆመችበት የቅራኔ መስመር፣ ከዐድዋ እና ሰገሌ የተዋረሱ መገለጫዎችም አጥልተውበታል። ልጅ እያሱ እና ተፈሪ መኮንን የፈጠሩት የሥልጣን መተጋገል፣ ኢትዮጵያውያን የተራረዱበትን የሰገሌ ጦርነት እንዳዋለደ ሁሉ፤ ኢሕአዴግ ውስጥ የነበረው ‘ፓዎር ስትራግል’ም እዛው ግንባሩ ውስጥ አለመቋጨቱ፣ አዝግሞም ቢሆን ወደ ጦርነት አምራቷል። የክስተቱን ከፊል ገጽታ የዚህ ዘመን “ሰገሌ” ያስመሰለውም ይህ ነው።

ዐድዋን የሚያስታውሰን ደግሞ፣ የሕወሓት ፍላጎት ሳይዘነጋ፤ ጦርነቱን ጫፍ-ካስረገጡት አጀንዳዎች የሚበዙት የውጪ ኃይሎች፣ በተለየ የአሜሪካ ኢንተረስት መሆናቸው ነው። ይህንን ጉዳይ ትንሽ ለማፍታታት የአሜሪካንን ፖሊሲዎች በመተቸት የሚታወቀው ፕ/ር Noam Chomsky እ.ኤ.አ በ2010 “Hopes and prospects” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ፣ ስለዩናይትድ ስቴትስ ያስነበበውን ጨርፈን እናስታውሰው፡- “የአሜሪካን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረታዊ መርህ ‘ሁሉም የእኛ ነው፣ ሁሉም ግን ሕዝባችን አይደለም’ የሚል ነው። ዓለም በአሜሪካ ብቻ ቁጥጥር ስር ይውላል። ከዚህ መርህ ጋር የሚጣረስ ምንም ዐይነት ጥያቄ አታነሳም። በዚህ ዓለም ላይ ሉዓላዊነትን በበላይነት የምትመራውና የምትቆጣጠረው አሜሪካ ብቻ ናት።”

ይህን ለማስፈጸም ደግሞ፣ ለስለስ ከሚሉት ውስጠወይራ የሰብዓዊ እና የዴሞክራሲ ተቋማት ፖሊሲዎቿ ጀምሮ ግብታዊነት የተቀላቀለበት የኃይል እርምጃ እስከ መውሰድ ትደርሳለች። በተለያዩ የዓለማችን ቁልፍ ቦታዎች ከ500 በላይ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያዎች አሏት። 24 ሰዓት ተጣራሽ መረጃዎችን ጭምር የሚግቱህ ግዙፎቹ ሚዲያዎችም፣ በ“አየር ወለድ”ነት ተሰልፈውላታል። የዓለምን ፖለቲካዊ እና ምጣኔ-ሀብታዊ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩት ተቋማትም “ተደራቢ አጥቂ” ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ናቸው።

ከሁሉም በላይ፣ የላቀ ጠቀሜታ ያላቸው ግን፣ በየአገሩ ሕዝባቸውን ለዕርድ አቅርበው የሚገብሩ መንግሥታት ናቸው። እንደ እነዚህ ዐይነት የፖለቲካ ቡድኖች ደግሞ በመላው ዓለም፣ በተለይ በአፍሪካ በገፍ ስለመኖራቸው ሲ.አይ.ኤን ጠይቅ?! የእነሱን ግላዊ ጥቅም ያከበረ በሙሉ “አለቃ” ነው። ዕርዳታ፣ የኢኮኖሚ እገዛ፣ የሁለትዮሽ ስምምነት፣ ሽብርተኝነትን መከላከል፣ የጤና ሽፋን፣ የንፁሃ ውሃ እና የመሳሰሉት አጀንዳዎችም፣ ረጃጅም ገመዶች ናቸው። ነጩ ቤተ-መንግሥት በፈለገ ጊዜ፣ አንዱን ወይም ሁለቱን መሳብ በቂው ነው። ሁሉም ስምምነቶች በውስጠ-ዘ “መታዘዝ” የሚል ትርጓሜ አላቸውና። የቅርብ ምስክር ካስፈለገ፣ በኢትዮጵያ ላይ ከአጉዋ መሰረዝ ጀምሮ በፕሬዚዳንት ባይደን እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን (ማቀቦችን) አስታውሳቸው?!

Continue Reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*