
ማኀበራዊ-ሚዲያ እና ባህሪው
የዘመኑ መገለጫ መረጃ-ቀዘፋ ነው። በእንግሊዝ አፍ “Cyber” ይሉታል። በመረጃ-ቀዘፋው ዓለም መረጃዎች፡- ለፖለቲካ፣ ለኢኮኖሚና ለማኀበራዊ ተግባራት ይውላሉ። ለተለያዩ ዓላማዎች፣ በተለያዩ ተዋንያን የሚለቀቁ መረጃዎች ዓለምን በድኀረ- እውነት (Post-Truth) ዘመን እንድታልፍ አስገድዷታል። መረጃን የማዛባትና የማምታታት (Disinformation) ውዥንብር የመፈጠሩ ኹነትም፣ ዓለም ላይ ሃሳዊነትን አንግሧል፤ (“Post-Truth” የሚለው ቃል እ.አ.አ. በ2016 በኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት መካተቱን ልብ ይሏል።)
ለዚህ ጽሑፍ መረዳት እንዲጠቅም ‹ዲስኢንፎርሜሽን› የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል ‹አምታች-መረጃ› በሚል የትርጉም ማዕቀፍ ውስጥ አስቀምጠነዋል። አምታች- መረጃን፡- ‹ተቀናቃኞችን ወይም ሌሎች ዒላማ የተደረጉ አካላትን ለማምታታትና እውነታን የተመረኮዘ ድምዳሜ ላይ እንዳይደርሱ ለማሳሳት ሆን ተብሎ ተቀነባብሮ የሚነዛ አሳሳች መረጃ› በሚል ብያኔ ልናፍታታው እንችላለን።
‹ድኀረ-እውነት› የሚለውን ቃል ደግሞ ሰዎች፡- ከጥሬ-ሐቅ ይልቅ፣ በስሜቶቻቸውና እምነቶቻቸው (አቋሞቻቸው) አኳያ የቀረቡላቸውን ማሳመኛዎች የመቀበላቸው ዝንባሌ ከፍ ያለበትን ሁኔታ ያንጸባርቃል። ከዚህ በመነሳት ዘመኑ ከፍትህ፣ ርትዕና እውነት ይልቅ፤ ተረት፣ ሀሰትና የሀሰት ዜና ገዢ መተርጎሚያ ሆነውበታል። በምድራችን ጨርሶውንም የሌሉ አገራት (ክልሎች) በሀሰት ይፈጠራሉ። በኑባሬ ያሉ ሕዝቦች ደግሞ ህላዊነታቸው ተመንፍቆ፣ የሉም ይባላሉ። በዳይ፣ በተበዳይ መከራ ተናጥቆ ያለቅሳል። ከጀርባ የወጋ፣ ለክህደቱ መሸፈኛና ለፈጸመው በደል፣ የ“ቃየል መስዋት” ያቀርባል።
ከላይ ለተጠቀሱት የቃላት ብያኔዎች ማስተርጎሚያ (የአምታች-መረጃዎች፣ የሀሳዊነት መገኛና ማስተንተኛ) በአመዛኙ ማኀበራዊ-ሚዲያው ነው። በአምታች- መረጃና በድኀረ-እውነት በምትናጠው ዓለም ጥሬ-ሐቅን ለመሸጥ፣ የመረጃ ጦርነት ባህሪያትን መረዳት የግድ ብሏል።
ዘመኑ ያፈራቸው የማኀበራዊ ግንኙነትና የመረጃ መለዋወጫ አውታሮች በርካታ በጎ ጎኖች ቢኖራቸውም፤ ተጓዳኙ አደገኛ ገፅታዎቻቸው መላው ዓለምን፣ በተለይ ‹በኢኮኖሚና በፖለቲካው ዳብረናል፣ ተቋማትን ገንብተናል› የሚሉትን አገራት በእጅጉ አስግቷል።
ማኀበራዊ-ሚዲያ፣ ከመደበኛው ሚዲያ (mainstream media) የተለየና ለቁጥጥር የማይመች ነው። በቀላሉ አጀንዳዎችን ለመልቀቅና በድብቅ ማንነት ለመጠቀም ከማስቻሉ በተጨማሪ፤ በጥቃቅን ወጪ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል የማስታወቂያ ሥርዐት ስላለው፣ ፖለቲካዊ ጫናው የጎላ ነው። በተለይ ‹ፖለቲካዊ ተግባቦት› በሚጎድላቸው ፓርቲዎች የሚመሩ አገራት፣ ለመረጃ ጦርነት ተጋላጭ ሆነዋል።
በፖለቲካ ተግባቦት ውስጥ የሶሻል-ሚዲያ ሚና እያደገ መምጣቱ ዓለማቀፍ ክሰተት ነው። ሚዲያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ደጋፊ ማስባሰቢያና የሲቪክ ማኅበራት ትኩረት የማግኛ መሣሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ዐዳዲሶቹ ሚዲያዎችም ምህዳሩን ከተቀላቀሉበት ጊዜ ጀምሮ ለመሰል ዓላማዎች ውለዋል። ይሁንና ዐዳዲሶቹ፣ ከመደበኛው ሚዲያ በተለየ መልኩ ብዙሃኑን በዕኩል ማሳተፉቸው እንደተጠበቀ፤ የሥነ-ምግባር መመሪያና ሙያዊ ኃላፊነት የሌላቸውን ‹‹ዜጎች›› የአሽከርካሪው ወንበር ላይ እንዲቀመጡ የፈቀዱ ናቸው። በውጤቱም ከአገራት ባለፈ፤ ቀጣናዊና ዓለማቀፋዊ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ነው።
Be the first to comment