
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ‹መንግሥት› የሚለው ቃል ከግለሰብና ከገዢ ፓርቲ ጋር መያያዙ የተለመደ ነው። ይህን ያደረጉት ሥልጣንን የግለሰብና የቡድን አድርገው ያስለመዱ አካላት ናቸው። አገሪቱም በአጭር ጊዜ ከዚህ አባዜ የምትወጣ አይመስልም። ይሄም ሆኖ፣ የመንግሥት ምስረታ አስፈላጊ ነው። ባለፉት ሦስት ዐመት በተቋም ደረጃ የተፈፀመ ዘረፋና ወንጀል ቢመረመር፣ ከምናስበው በላይ ማስደንገጡ አይቀርም። ትሕነግ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ኮትኩቶ ያሳደገው ካድሬ፣ አሳዳጊው በዝባዥ ድርጅት ሲነቀል ከመመልከቱ በተጨማሪ፤ በምትኩ ሌላ ሲመጣ መታዘቡ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ቋሚው ስርቆት እንጂ፤ ሥልጣን ላለመሆኑ የተግባር ትምህርት ሆኗታል። ከ2010ሩ ለውጥ ወዲህ ግዘፍ-የሚነሳ የስርቆት ዐይነትን ያበራከተውም ይህ ነው። አንዳንዶቹ ተቋማዊ ባህሪ ተላብሰው ታይተዋል። ያለጨረታ ሜጋ ፕሮጀክቶችን መስጠት፣ የመሬት ቅርምት፣ የመንግሥት ንብረት ግዥና ህንጻ ዕድሳትን ጨምሮ፤ በተለያዩ ሰበቦች የሕዝብ ሀብት ተመዝብሯል። የቀደመውን ውርስ መሠረት ባደረገ መልኩ፣ ባለፉት ሦስት ዐመት ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ፣ የስርቆት ውድድር ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ንግግር ላይ ሌብነትን የሕልውና አደጋ አድርገው ሲያቀርቡ ገፊ-ምክንያታቸው የሦስት ዐመቱ የስርቆት ውድድር፣ የመንግሥታቸው መታነቂያ ገመድ መሆኑን ስላመኑ ይመስላል። በተለይ እሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ የቀደመውን በሚያስንቅ ሁኔታ፣ በየመንግሥት መስርያ ቤቱ ስርቆት አለቅጥ ተንሰራፍቷል። ‹መንግሥት የለም› ብሎ በገቢር የሚያምነው ራሱ ዘራፊው ካድሬ ሆኖ ከርሟል። በክልሎች ያለው ካድሬ ከጉቦና ስርቆት በተጨማሪ፤ የጦር መሳርያ ዝውውር ውስጥ ገብቷል። ሰው በሚታገትባቸው አካባቢዎች የማስለቀቂያ ገንዘብ የሚቀበል ጭራቅ ካድሬ ተፈጥሯል። “የተመረጠ መንግሥት የለም” የሚለው፣ በተግባር ትሕነግ ባሳደገው ካድሬ ብሶ ከርሟል። ብልፅግና-መሩ መንግሥት፣ ይሄን ሌብነት ይቀርፈዋል የሚለው አጠራጣሪ ሆኖ፤ በካድሬው ዘንድ ሳይቀር መንግሥት አልባነት ታምኖበት የቆየ መሆኑ ግን አይካድም።
ወቅቱ የጦርነት ነው። ጦርነት የሚመራው ደግሞ በተቋማት ጥንካሬ ነው። በግንባር የሚዋጋውን ሠራዊት ለመምራት፣ ሎጀስቲክሱን ለማሳለጥና ዐዲስ የሰው ኃይል ለመመልመል፣ ከግንባር ባሻገር የዲፕሎማሲ ውጊያው ላይ ብልጫ ለመውሰድ… ተቋማት ግዴታ ያስፈልጋሉ። በሌላ በኩል መንግሥት እንዳይመሰረት የሚፈልጉ አካላትም፣ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ሙሰኛም፣ ክፉም መንግሥት ቢሆን ቢያንስ ለሥልጣኑ ሲል “ጦርነቱን ይመራል” በሚል የቻሉትን ያህል ለማደናቀፍ ጥረዋል።
Be the first to comment