
እ.ኤ.አ የ2014ቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማት ማስፋፊያ ፕላን ይፋ መደረግን ተከትሎ፣ በመላው ኦሮሚያ በተቀሰቀሰው የተቃውሞ እንቅስቃሴ፣ በሕወሓት ሹፍርና ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የነበረው ኢሕአዴግን ክፉኛ መናጡ አይዘነጋም። ሕወሓት የአናሳ ብሔር ወኪል ሆኖ ሳለ፤ ነገድን መሰረት ያደረገ መንግሥታዊ የሥልጣን ክፍፍልን የሚከተል ሥርዐት መመስረቱ፣ አፍኖና ጨፍልቆ አየበዘበዘ ለመኖር የማለሙን እውነታ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። የሆነው ሆኖ፣ ይህ የተቃውሞ ትግል ተፋፍሞም ከብዙ መስዋዕትነት በኋላ፣ ዳግም በአገራችን ብሩህ ተስፋን እንድንሰንቅ ያስቻሉንን የዛሬውን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሥልጣን ማምጣቱ ይታወሳል። አብዝተው አገራዊነትን ያቀነቅኑት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ይወሰዱት በነበረው የትኛውም ዐይነት ተግባራት፣ ዓይኑ መቅላት የጀመረው ጎጠኛው ሕወሓት ደግሞ ወደ ማኩረፉ አዘንብሏል።
በርግጥ ሥልጣን በጁ እስካለ አፍኖና ጨፍልቆ እየበዘበዘ አልያም ቀሪውን ባለ አገር ለመከራ ጥሎ ሀገረ- ትግራይን የማቋቋም የሰነበተ ክፋትን ለሰነቀው ይህ ቡድን፣ ድንገት ከአራት ኪሎ መገፋቱ ቢያስኮርፈው የሚገርም አልነበረም። ቡድኑ በኩርፊያ ብቻ ሳይገታ፣ መቀሌ አድፍጦ እንዴት ነገሮችን መቀልበስ እንደሚችል ማሴሩን ተያያዘው። ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና መንግሥታቸውንም በሆነ ባልሆነው ክፉኛ ያብጠለጥል ጀመር። አስተዳደራቸውም እንዳይጸና፣ በመላ አገሪቱ ትርምስ መደገስን ሥራዬ ብሎ ተያያዘው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው በሚታደሙባቸው ሕዝባዊ መድረኮች አንዳንዴ በሽሙጥ፣ ሲገፋ በሃላል ወደ መዛለፉ ገቡ። ይህ ብስለት የራቀው የሁለት ወገን እንኪያ ሰላምትያ እየተካረር ሄዶና የሽቅብ-ቁልቁል የሥልጣን ተዋረድ ከመሆን አልፎ፤ አግድም፣ በተለይ የዐማራ ክልላዊ መንግሥትን ያሳትፍ ጀመረ። ኢትዮጵያን ለግማሽ ክፍለ ዘመን ሲያደሟት አፍላ እድሜያቸውን የገፉት አዛውንቱ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቄም መለስ ቀለስ ማብዛት፣ በፌደራል መንግሥቱ እና ሕወሓት መካከል ለነገሰው የቀዝቃዛ ጦርነት ጡዘት፣ የበኩሉን አሉታዊ አበርክቶ ማድረጉ የሚካድ አይደለም።
ኮቪድ፣ ምርጫ፣ የወጣቱ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እና ሌሎች ምክንያቶችም ቀዝቃዛውን ጦርነት Catalysed ማድረጋቸውም በግልጽ ነበር። የነገርዬው አካሄድ መጨረሻ የለየለት የእርስ-በርስ ጦርነት የመሆኑ እውነታ የቀን ጉዳይ እንደሆነ፣ ለሁሉም ግልጽ ነበር። ቀኑም ደርሶ፣ ፊሽካው በሕወሓት ተነፋ። በአጸፋውም የፌደራል መንግሥቱ ሰገባውን መዘዘ። የተፈራውም ሆነ። ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቄም ሰርግና ምላሽ ሆነላቸው። በአጋጣሚውም በቀላቸውን ተወጡ።
Be the first to comment