የሰሜኑ ጦርነት (በፖለቲካ እስረኛው መነፅር) | በእስክንድር ነጋ – ከቂሊንጦ

ፈረንጆቹ fateful የሚሏቸው ሦስት ጥያቄዎች ፊት ለፊታችን ተደቅነውብናል። እንደ አገር እጣ ፋንታችን የሚወሰንባቸው ናቸው። በመጀመሪያ፣ የሰሜኑ ጦርነት ወታደራዊ መፍትሄ አለው ወይ? የሚለው አለ። ከዚያም፣ የሰሜኑ ጦርነት በድርድር ሊቆም ይችላል ወይ? በመጨረሻም፣ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ምን መደረግ አለበት? የሚለውን እናገኛለን።

ከእነዚህ ውስጥ፣ የሰሜኑ ጦርነት በድርድር ሊፈታ ይችላል ወይ? የሚለውን ብቻ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

ፈረንጆቹ “Sense of invincibility” የሚሉት ነገር አለ። ወደ ዐማርኛ ስንመልሰው፣ “የአይሸነፌነት ስሜት” ልንለው እንችላለን። ይህ ከተራው የአሸናፊነት ስሜት ይለያል። በምን? የሚለውን ወደኋላ እመለስበታለሁ። ለጊዜው፣ የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሳኔ ያስከተለውን እንደምታ እንመልከት።

በመንግሥት በኩል የተላለፈ የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሳኔ በሁለት መንገድ ተግባራዊ ሊሆን ይችል ነበር። አንደኛው፣ ጦሩ ትግራይን ሳይለቅ፣ ይዞታዎቹን እየተከላከለ ከጥቃት መቆጠብ ሲሆን፣ ሁለተኛው የጦርነት ቀጠናውን ሙሉ ለሙሉ በመልቀቅ ይሆናል። እንደሚታወቀው፣ መንግሥት ሁለተኛውን አማራጭ ተግባራዊ አድርጓል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት፣ እውነትም ትግራይን ሙሉ ለሙሉ የለቀቁት አስገዳጅ ወታደራዊ ሽንፈት ባልደረሰበት ሁኔታ ከነበረ፣ ከአገራችን የደርግን፣ ከውጭው ዓለም የናፖሊዮንን ውድቀት አላጤኑም ማለት ነው። ደርግ፣ ትግራይን ሙሉ ለሙሉ በመልቀቅ ጦርነቱን ትግራይ ውስጥ ማስቀረት አልቻለም። እነ ዐቢይ ይህን ተሞክሮ ግምት ውስጥ ያስገቡ አይመስልም።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የጦር ጄኔራሎቻቸውን ይስሟቸው አይስሟቸው አላውቅም እንጂ፣ የናፖሊዮን አወዳደቅ ከጄኔራሎቻቸው የተሰወረ ሊሆን አይችልም። በተጋነነና ቁጥሩ በተዛባ መልኩ፣ ሆኖም ግን እንደ እኔ ዐይነት ወታደር ያልሆነ ሰውም ሊገባው በሚችል ደረጃ ሲነገር፣ ናፖሊዮን 600,000 ጦር ይዞ ሩሲያን ወረረ፣ 60,000 ሰው ይዞ አፈገፈገ፣ 6,000 ሰው ይዞ መናገሻው ወደሆነችው ፓሪስ ገባ ይባላል።

Continue Reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*