የሶሪያው የአሜሪካ ፖሊሲ፣ በኢትዮጵያ? | ዶ/ር ሔሮን ገዛኽኝ

በው “የወደቀ እንጨት ምሳር ይበዛበታል” እንዲሉ፤ ወትሮም አንገቷ ራሷን መሸከም ተስኖት ከወዲህ ወዲያ የምትላጋዋን ኢትዮጵያችንን፣ ጨርሶ ከመሬት ሊጥሏት እና በውድቀቷ የገንዘብ ከረጢታቸውን ለመሙላት የሚያንዣብቡ አሞራዎች በርክተውባታል። በርግጥ አገሪቱ ከዚህም ከዚያም በሚገፏት ክፉዎች አደገኛ ውክቢያ ውስጥ ከገባች ውላ አድራለች። የBroken Window The­ory ጽንሰ-ሃሳብ ጭብጥን ከዓለም ዐቀፍ የፖለቲካ ሳይንስ ትንተናዎች ጋር ያዛመዱ ባለሙያዎች፣ ይህንን የአገራችን ምሳሌያዊ አነጋገር ይጋሩታሉ። ንድፈ ሃሳቡ፣ ቀን ፊቷን ስለምታዞርባቸው አገራት ተገማች መከራ የሚያትት ነው። ሊቁም ደቂቁም እንደሚነሱባቸው ያረዳል። ኢትዮጵያም ዛሬ እንዲህ ባለው ፈተና ውስጥ ወድቃለች። ለዚህ ደግሞ የምዕራባውያኑ ቅጥ-ያጣ ዲፕሎማሲያዊ ጫና፣ የግብጽ የእጅ አዙር ጣልቃ ገብነት እና የሱዳን ወረራ ተጠቃሽ ናቸው። ቀደም ሲል ደመኛ የነበሩ እና አገርን ለውድቀት የመዳረግ ተገማች ዐቅም ያላቸው፣ የአገር ውስጥ የፖለቲካ ተዋንያንም የመሳሳብ ዝንባሌ እዚህ ጋ ሳይጠቀስ አይታለፍም።

የሕወሓት ወንበዴ ታጣቂዎች ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የሰነዘሩትን አኩይ ጥቃት ተከትሎ፣ በፌደራሉ እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥታት መሃል፣ ከሁለት ዐመት በላይ ያስቆጠረው ፖለቲካዊ ውጥረት ወደ ለየለት አውዳሚ ጦርነት ተሸጋግሯል። ይህም የጦርነቱ አውድማ የሆነችውን ትግራይን ለሁለንተናዊ ቀውስ ከመዳረጉ በዘለለ፤ አገሪቱን ለከበደ የሕልውና አደጋ ማጋለጡ አሌ የሚባል አይደለም። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በጦርነቱ የመጀመሪያ ሳምንታት ሕወሓትን ክፉኛ በመደቆስ የተቀናጀው አስደማሚ ወታደራዊ ድል እና ፍጹማዊ የበላይነትም ኋላ ላይ መንገራገጭ እንደገጠመው መናፈስ ከመጀመሩ በላይ፤ መንግሥት “ፖለቲካዊ…” ብሎ በጠራው ውሳኔ ሠራዊቱ ትግራይን ለቆ እንዲወጣ አዝዟል። ይህ ደግሞ ጦርነቱ ሌላ መልክ እንዲይዝ ማድረጉን ብዙዎች ይስማማሉ። በተለይ ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ወደ አጎራባች የአፋር እና የዐማራ አዋሳኝ ቦታዎች መሸጋገሩን እንደ ማሳያ ይጠቅሳሉ።

Continue Reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*