
ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ሰኞ ጠዋት፣ ጠቅላላ ምርጫው በምልዓት የተጀመረ ይመስለኛል። ለቀኑ ውሎዬ ያሰናዳሁትን ‹ማቴሪያል› ይዤ ወደ ምርጫ ጣቢያ ያመራሁት ከማለዳው አስራ ሁለት ሰዓት ነበር። በርግጥም እኔ መንገድ በጀመርኩበት ሰዓት የአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎች የተወረሩ ይመስል ፀጥ-ረጭ ብለዋል። ለወትሮው የሚጣደፈው መኪናም ሆነ ሕዝብ የለም። እንዲህ በፀጥታ የሰከነችውን የከተማ ገጽታ እየቃኘሁ፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 17 ደረስኩ።
በምርጫ ክልሉ ሥር በሚገኘው ወረዳ ዘጠኝ ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች በተራራቀ ቦታ ላይ ተተክለዋል። የጣቢያዎቹን ዙሪያ-ገብ እያፈራረቅሁ ስመለከት፣ ለመምረጥ የተሰለፈው ሕዝብ በሁለት ዙር ረዝሟል። በምዝገባ ሰሞን የሰማሁት ‹የመራጭ አልተመዘገበም› ወሬ እንደ ጉም የበነነ መሰለኝ። በርግጥ፣ ከአስር ሚሊዮን በላይ ከሚገመተው የከተማዋ ሕዝብ መካከል፣ የምርጫ ካርድ የወሰደው በጣም ትንሽ መሆኑን ሰምቻለሁ። በአገር ዐቀፍ ደረጃም እንዲሁ፣ ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሚገመተው ሕዝብ ውስጥ ሰላሳ ስምንት ሚሊዮን የሚሆነው ዜጋ ካርድ መውሰዱ ተነግሯል።
በወቅቱ ከካርድ አወሳሰዱ ችግር አኳያ ምርጫው ከድምጽ መስጫው ቀን በፊት የተጭበረበረ የሚመስል ሁኔታውን የሚናገሩ ብዙ ነበሩ። ይህም ሆኖ፣ ካርድ ያወጣው ዜጋ ድምፁን ዋጋ ለማስገኘት ያደረገው ጥረት ኢትዮጵያዬ የቀራትን ጭላንጭል ተስፋ ዋጋ ሰጥቶ አልፏል። አገሬ ተዓማኒነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ባይቀናትም፤ ምርጫ ማካሄዷ ራሱ እርግማንና በረከት አለው። እርግማኑ፣ ተወዳዳሪ ፖለቲከኞች ውጤት ከተነገረ በኋላ የቁጣ በትራቸውን ማሳረፋቸውን ታሪክ ከመናገሩ ጋር ይያያዛል።
Be the first to comment