
በኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ ሰባት ዐመታት ያለ ትግራይ ልሂቃን ይሁንታ የሚፈፀም አንዳችም ጉልህ ነገር አልነበረም። ራሳቸውን የአገሪቱ ልዩ ተቆርቋሪ አድርገው ሲሾሙ፤ ሌላውን ዜጋ ልዩ ተጠርጣሪ አድርገው በመፈረጅ ነበር፣ በሥልጣን መቆየቱ ሙዝ እንደመላጥ የቀለላቸው። የአፍ-መፍቻ ቋንቋም ከዐውዱ ተነጥሎ ከመግባቢያነት በዘለለ፤ ለማስፈራሪያነት ውሏል። ቋንቋን የተንተራሰ የገቢ ኢ-እኩልነትም ተተክሎ ሰንብቷል። የዚህ አድሎኛ ሥርዐት ቀማሪዎች ደግሞ የትግራይ ልሂቃን ናቸው። አገሪቱን በጅምላ ጠቅልለው፡- የሥልጣን ቦታዎችንና የኢኮኖሚውን መስክ ከመቆጣጠራቸው በተጨማሪ፤ ያልገቡበት ማኀበራዊ ተቋማት አልነበረም። ይህ ደግሞ፣ 6 ከመቶ ያልተሻገረ ውክልና ይዘውም፣ 94 ከመቶውን ኢትዮጵያዊ የበታች አድርገው እንዲገዙ አስችሏቸዋል። በዚህም፣ ደም ያልፈሰሰበት የኢትዮጵያ ግዛትም ሆነ ብሔር የለም። በተለይ ዐማራ ላይ የበዛ የጠላትነት ሲሜት ቢኖራቸውም፤ ተነግሮ የማያልቅ ጭፍጨፋ ያደረሱበት ቢሆንም፤ ደም ያልተቃቡት የኢትዮጵያ ብሔር አለመኖሩ ይታወቃል። ይህ ነው፣ ደመኛ ያበዛባቸውም።
በጥቅሉ፣ በአገዛዝ ዘመናቸው ኢትዮጵያን ኪሳቸው የከተቱ ያህል መብትና ብሔራዊ ጥቅም፣ እነሱ ለፈልጉት ቆንጥረው የሚሰጡት እንጂ፤ በዜግነት የሚገኝ እንደሆነ ሳይገባቸው ተሰናብተዋል። የትግራይ ልሂቃን፣ ቢያንስ ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ ዴሞክራሲን መለማመድ ቢችሉ ኖሮ፣ ቅድመ-1983፡ – ከሁመራ እስከ ሞያሌ፣ ከሰመራ እስከ ጋምቤላ… ኑሮን ለማቃናት የሄደውን፣ በሥርዐቱ ተጠቅሞ ቱጃር የሆነውን የትግሬ የኢኮኖሚ ትስስር አጠናክሮ ማስቀጠሉ በቀለላቸው ነበር። እነሱ ግን በአንድ በኩል፣ በግዛት ተስፋፊነታቸው ወልቃይትና ራያን በጉልበት ሲጠቀልሉ፤ በሌላ በኩል፣ በመላ ኢትዮጵያ በዘረጉት የአናሳ አምባገነናዊ ሥርዐት አንብረው አዛዥ-ናዛዥ የሆኑበትን አፓርታይዳዊ አገዛዝን መከተል መርጠዋል።
የሆነው ሁሉ ባይሆንና በእኩልነት አምነው ዴሞክራሲን የመለማመድ ሥርዐት ተክለው ቢሆን ኖሮ፤ ከመንበራቸው ከመፈንገላቸው ሌላ፣ እንዲህ የተጠሉበት ክፉ-ዕጣ ባልገጠማቸው ነበር። ይሁንና፣ በአናሳነት ስሜት እየተሰቃዩ፣ በቁስ ሰቀቀን ተዘፍቀው በዓይናቸው ያዩት ሥልጣንና ሀብት በሙሉ መጥፊያቸው ሆነ። ትግሬ ልዩ፣ ጀግና፣ በብቸኝነት ኢትዮጵያን ለመግዛት የተቀባ አድርገው ትርክት ፈጠሩ። “እንወክለዋለን” ያሉትን አብዛኛውን ሕዝብም፣ በተለይ ወጣቱን የአስተሳሰባቸው ተሸካሚ አድርገው አሳመኑት። ለሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ፣ ከእነሱ በቀር፣ ማንም ማስተዳደር እንደማይችል ሰብከው ሲያበቁ፤ ወደ ሥልጣናቸው የሚጠጋውን ሁሉ በመለኮታዊ ኃይል የሚቀሰፍ እስኪመስል ድረስ ትርክቱን አሰፋፉት። ራሳቸውንም በአፍሪካ አቻ-የለሽ የሽምቅ ተዋጊ እስመስለው፣ በውጭ አገር ሰዎች ሳይቀር ውዳሴዎችን በማጻፍ፣ በርካታ ዶክመንተሪዎችን በማዘጋጀት፣ ‹ልዩ ነን› የሚል የሥልጣን አጥር ለመፍጠር አብዝተው ደከሙ። ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማስፈራራት የፈጠሩት ትርክት፣ እነሱን ጠልፎ ጣላቸው።
Be the first to comment