
ይህ መጽሐፍ በኢትዮጵያችን የአገር ግንባታ ውስጥ የ19ኛው መክዘ ሁለተኛ አጋማሽ ወዲህ እስከ ዘመኑ መባቻ ድረስ ግንባር ቀደም ብሔራዊ ጀግና በሆነው በራስ ጎበና ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። በርግጥ ጸሐፊው የታሪክ ባለሙያ ቢሆንም፤ ባለታሪኩን በመምረጡ ብቻ የሚያስመሰግነው ነው።
እንዳለመታደል ሆኖ ግን መጽሐፉ መሠረቱን ውጪ ባደረገ አሣታሚ የታተመ በመሆኑ፣ ለአገር ውስጥ ገበያ ገና አልቀረበም። የፀሐይ አሣታሚ ባለቤት ኤልያስ ወንድሙ በርካታ በኢትዮጵያ ጉዳይ የተጻፉ መጻሕፍትን እና ጥናታዊ ጽሑፎችን አሳትሞልናል። በተባራሪ የደረሱንን እና በጣም ጥቂቶቹን አገራችን ላይም ታትመው ለማንበብ ችለናል። ለዚህም ምስጋናችን ትልቅ ነው። ነገር ግን በራሳችን ጉዳይ፣ በራሳችን ጸሐፊ እና በራሳችን ቋንቋ የተዘጋጁ ሥራዎችን በአገር ውስጥ ታትመው ለማንበብ የማንችልበት፣ ብናገኝ እንኳን ደጅ የምንጠናበት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ያስወቅሰዋል።
በውጪ የተመሠረቱ አሣታሚ ኩባንያዎች ለምን ቅድምና እንደሚሰጡ ቢገባንም፤ ዛሬ እንደምናየው ዐይነት መጽሐፍንም የሚተኙበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። ራሳቸውን ብቻ በሚመለከቱ አሣታሚዎቻችን ምክንያት ጸሐፊዎቹ ማቅቀው ባዘጋጁት ሥራ ተጠቃሚ የማይሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ አንባቢውም ለማግኘት የማይችልበት እና ሁሉ ነገር በእነርሱ በጎ ፈቃድ ብቻ የሚወድቅበት ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መምጣቱ አሳሳቢ ነው። የእኔ ጽሑፍም የአሣታሚውን ዝንጋታ ለመተቸትም፤ መጽሐፉ ቶሎ አገር ውስጥ ታትሞ ፍሬ ነገሩ የውይይት አካል እንዲሆን ለማትጋትም ነው።
ከዚህ መጽሐፍ ፋይዳ መካከል ስለባለታሪኩ ያለውን ውሱን ዕውቀት ለመግፋት ያደረገው ጥረት እና ፖለቲከኞች ስለባለታሪኩ ያለውን አረዳድ ለማልኮስኮስ ያደረጉትን ጥረት ለማረቅ የሄደበት መንገድ ነው። በመጀመሪያው ጉዳይ መጽሐፉ አራት ክፍሎች አሉት። የመጀመሪያው ስለጥናቱ ዳራ የቀረበባቸው ሁለት ምዕራፋትን ይዟል። ሁለተኛው ክፍል ስለልጅነቱ እና ወጣትነት ጊዜ፣ ከምንሊክ ጋር ትውውቅ እና እስከ ራስነት የደረሰበት ማዕረግን የተመለከተ ነው።
Be the first to comment