
በአጉል ጭብጨባ እና በተራ መሞጋገስ በደመቀው የብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤ ላይ አንድ የተሰማ ልዩ ድምጽ ነበር። የአፋሩ የብልጽግና ሰው የአደን ፋራህን በእጩነት መቅረብ ሲቃወም ታዝበናል። የተቃውሞው ይዘት እጅግ ጠንካራ እንደነበረም አስተውለናል። የራሱን ፓርቲ ሁለተኛ ሰው፣ “በሕዝቦች መካከል ግጭት በማስነሳት” ሲል ከስሶታል። ምናልባት የፓርቲውን ሊቀ-መንበር ጨምሮ፤ ሌሎች ዴሞክራቶች “ተቃውሞው መቅረብ ዴሞክራሲያዊ ነው” ብለው ያልፉት ይሆናል። ለእኔ ግን እንደዚያ አይደለም። በቀጥታ ስርጭት በሚተላለፍ የገዥ ፓርቲ የአመራር ምርጫ ላይ፣ ሊያውም በምክትል ሊቀ-መንበር እጩነት ላይ ይሄንን ዐይነት ቅሬታ ማሰማት ብዙ ችግሮች ለመኖራቸው ፍንጭ ይሰጣል።
ወቅታዊውን የአፋር ውሎና አዳር በዚህ ላይ ስናክልበት ደግሞ ለበለጠ ጥርጣሬ ይዳርገናል። ክልሉ በሕወሓት ጦር እየደረሰበት በሚገኘው ያልተቋረጠ ወረራ፣ ትንኮሳና ውድመት፣ “እውነት መንግሥት ከአፋሮች ጋር ነውን?” የሚያስብል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል። ይሄ ቅሬታ የየሶሻል ሚዲያው ወሬ መሆኑን ማስታወስ ግድ ይላል።
በቅርቡ ከአዎል አርባ ጋር ፎቶ ለለቀቀችብን የአሜሪካዋ አምባሳደር፣ “ሕወሓትን ከወረርካቸው የአፋር ወረዳዎች ውጣ?” ማለት ስለምን ከበዳት? ለመሆኑ፣ ፓርቲውም ሆነ መንግሥት ከአፋር እና ከአፋሮች ጋር በዚህ ደረጃ መገፋፋት አለባቸው ወይ?
ታሪካዊና ወቅታዊ ስህተቶችን አርሞ፣ በተጠና እና በተደራጀ መልኩ ከአፋሮች ጋር መሥራት ይቻለን ዘንድ በዚህች አጭር ማስታዎሻ አንዳንድ ነጥቦችን አነሳለሁ።
“የፕሮፌሰሯ ቅኝት”
ሰሞኑን ፕሮፌሰር Ann Firtz-Gerald ወደ አፋር ተጉዛ “The Forgotten Conflict in Ethiopia: Afar’s Northern Communities” የሚል ጠቃሚ ማስታወሻ ትታልናለች። “አፋርን ዓለም ረስቶታል” ትላለች ፕሮፌሰሯ። ‘መንግሥት ረስቶታል’ ላለማለት
የምትጠነቀቅም ይመስላል። ሕወሓት ‹ተከብቤያለሁ› ቢልም፤ ረዥም ድንበር በሚጋሩት አፋር እና ትግራይ መካከል ምንም የመከላከያ ሠራዊት እንደሌለ ትመሰክራለች። በክልሉ ተዘዋውራ በርካቶችን አነጋግራ በሠራችው በዚህ ዘገባ ውስጥ፣ ሕወሓት እስከ 100 ሺሕ በሚደርስ ወራሪ ኃይል የአፋርን ሰሜናዊ ወረዳዎች መያዙንም ትነግረናለች። የወረራውን ጊዜና ሁኔታም ታብራራለች።
Be the first to comment