
የዐድዋ ድል ‘የዓለምን ታሪክ ገልብጧል’ ይባላል፤ አዎን። ‘የአውሮጳውያንን ውርደት በመላው ዓለም እንደ ርዕደ መሬት አንዝሯል’ ይባላል፤ ይህም ልክ ነው። ‘ድሉ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራትና ጌጥ ሆኗል’ ይባላል፤ ሁላችንንም ያስማማናል። ሆኖም የዐድዋ ጦርነት የተከወነው የኢትዮጵያና የጣልያን ወታደሮች በያዟቸው ጠመንጃዎች መሃል ብቻ አልነበረም። እንደ ሌሎች የዓለማችን የጦርነት ታሪኮች ሁሉ፣ የዐድዋ ጦርነትም ዓበይት ትኩረቱን ያደረገው በባሩድ ዙሪያ ይሁን’ጂ፣ ከምድሩም ጋር ነበር። ይህ ጽሑፍ ከምድሩ ጋር የተደረገውን ፍልሚያ በጊዜና በቦታ ለይቶ በመፈተሽ፣ የተደረሰበትን ድምዳሜ በአጭሩ ለማሳየት ይሞክራል።
ፍልሚያው ባሩድ ብቻ?
ጦርነቱ በተካሄደበት ወቅት የከባቢውን ሁኔታ በበቂ ሁኔታ መርምሮ የዘገበ ባለሞያ አልነበረም። አለመኖሩም አይደንቅም። ክፍተቱ ግን፣ ለአንዳንድ ጸሐፊያን የተሳሳቱ ድምዳሜዎች “የማሪያም በር” ከፍቶላቸዋል። ለዚህም ነው የጣሊያን ጦር ከተሸነፈባቸው ምክንያቶች አንዱ ‘ፍልሚያ የተካሄደበት መሬቱ፣ ለኢትዮጵያውያን የበለጠ አመቺ ስለነበረ’ የሚል እንቶ ፈንቶ የምናነበው። “ታሪክ እንደ ጦርነት ያሉ ክስተቶችን ሲከትብ፣ ምድሩ ለመጻፊያ ሰሌዳነት ያገለግላል (History focuses on events such as wars that are inscribed in geographic space)’ ይባላና፤ የዐድዋ ዘመቻን የዘገቡ ጸሐፍት እግረ መንገዳቸውን የጉዞውንም ሆነ ፍልሚያ የተካሄደበትን የምድር ሁኔታ በተወሰነ መልኩ ገልጸውት እናገኛለን። ይህ መረጃ የሣሣና በወጥነት ያልተመረመረ ቢሆንም፤ አሁን ለቀረበው ጥናት እንደ እርሾ ሆኖ አገልግሏል። ባናቱ ደግሞ የምድር መረጃ ማጠናቀሪያ ዘዴን በመጠቀም፣ ተዛማች መረጃዎችን ከስፍራው ጋር አነባብረን መርምረናል።
አድዋን ምኒልክን ዘንግቶ ማክበር ተቀባይነት የለውም