
እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች “Back to square one” የሚል ተስፋ መቁረጥን የሚያመለክት ብሂል አላቸው። ይህ ቃል እኛ የገጠመን ሂደትን ለመግለጽ ተቀራራቢ ነው። ወደአማርኛ ስናመጣው፣
ከከባድ ውድቀት በኋላ ወደነበሩበት መመለስ ወይም ከዜሮ መጀመር የሚል አቻ ትርጉም ይሰጠናል። በርግጥ፣ ሁኔታችን በዚህች አጭር አረፍተ ነገር የሚተነተን አይደለም። ከዚህም ይከፋል። የ”ለውጡ” መንግስት የተጓዘበትን የአራት ዓመት መንገድ ለማብራራት “The great leap backward” የሚሉት ቃል የተሻለ ይሆናል። የገጠመንን አስፈሪ ቁልቁለት በዋዛ ያዝነው እንጂ እውነትም “ታላቁ መንሸራተት” ትክክለኛ ቦታውን የሚያገኘው በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ነው። ከድንግዝግዝ ወደጨለማ፣ ከጣር ወደሞት የሚደረገውን ፈጣኑን ጉዞ ያለፉት ጥቂት ዓመታት አሳይተውናል።
ከየት ወዴት?
ጠ/ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ወደስልጣን ከመምጣታቸው ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ የነበርንበትን ሁኔታ ብዙዎቻችን የምንዘነጋው አይደለም። ከሁለት አስርታት በላይ ቀጥቅጦና ረግጦ የገዛው ሕወሓት/ኢሕአዴግን ለመጣል ብርቱ ሕዝባዊ ትግል ይደረግ ነበር። ይህንን የጭንቅ ወቅት ጨምሮ ከዚያ በፊት በነበሩት 26 ዓመታት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን 180 የሚሆኑ መግለጫዎችን አውጥቷል። ከዚህ አሀዝ ውስጥ 40 ገደማው የብሔር ግጭቶችን ተከትለው የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን የሚመለከቱ ነበሩ። ምናልባት፣ የያኔው ኢሰመኮ በጊዜው ስርዓት የተጠለፈ በመሆኑ የተጠቀሰውን ቁጥር እንጠራጠር ይሆናል። የማይታበለው ሀቅ ግን፣ በመግለጫዎቹ ከተጠቀሱት ግፎች መካከል አብዛኞቹ የተፈጸሙት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መሆኑ ነው።
ይህ ታሪክ የተቀየረው የ”ለውጥ” ኃይሉ ወደስልጣን ከመጣ ብዙም ሳይቆይ ነው። ምሳሌ ለመጥቀስ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ስር በምትተዳደረው ጌዲኦ ዞን የተፈጠረውን አጋጣሚ እናንሳ። በወቅቱ 31 ንጹሐን በአሰቃቂ መንገድ ተገድለዋል። ምክንያቱ ደግሞ፣ መንግስት ለዜጎቹ በቂ ጥበቃ ባለማድረጉ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ባወጣው 143ኛ መግለጫ ላይ በተገቢው ቃል ተብራርቷል። በሐረር ከተማ፣ የአፍረንቀሎ ባህልና ታሪክ ማዕከል ለመገንባት በነበረው ዝግጅት ላይም የኦሮሚያና የሐረሪ ክልል ፕሬዘዳንቶች በተገኙበት
ግጭት ተነስቶ ነበር። እኚህ ሁለት የአንድ ቀን ክስተቶች የተፈጠሩት ጠ/ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ቃለመሀላ በፈጸሙ በ28ኛው ቀን ነበር። ያኔ “መንግስቱ ስላልረጋ፣ ከባለፈው ስርዓት የወረደ ክፉ ውርስ፣ ረዥሙ የሕወሓት እጅ” በሚሉ ሰበቦች አስደንጋጩን ክስተት አይተን እንዳላየ አለፍነው። አሁንስ? የአሁኑ ጉዳት በብዙ እጥፍ ጨምሮ ቦታ ብቻ እየቀያየረ በሁሉም ጓዳ ገብቷል።
Be the first to comment