ፋኖ እንደ “አበጀ በለው” | መኩሪያ አያሌው

አበጀ በለው በ“ፍቅር እስከ መቃብር” ልብ ወለድ ውስጥ ወደር የሌለው ፍፁማዊ ጀግና ገፀ ባህሪ ነው። ደራሲው በእርሳቸው ዘመን ሊገልጡት የፈለጉት እውነት መልኩ ይለያይ እንጂ፤ በዘመኔ ባህሪው ተመሳሳይ ነው። የፊታውራሪ መሸሻን ከልክ ያለፈ የሰው ንቀት (እሳቸው ደግሞ አገሬውን “ባላገር” ይሉታል)፣ አልጠግብ ባይነት፣ ራስ ወዳድነት፣ ጉራ፣ ጀግንነት እና የአባ ሞገሴን አድር ባይነት (አስመሳይነት፣ ከንቱነት)…፤ በሌላ በኩል ደግሞ የጉዱ ካሳን የሞራል ልዕልና፣ የቀኝ አዝማች አካሉን በሳል አማካሪነት፣ አስተዋይነት፣ እምነት (ምንም እንኳ ፊትውራሪ መሸሻ በጥርጣሬ ቢመለከቷቸውም)፣ የአበጀ በለውን ጀግንነት እና የመሳሰሉትን በፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ የተሳሉትን አስገራሚ ገፀ ባህሪያት በአትኩሮት ሳስባቸው የእኔም ዘመን መራራ ተንቀሳቃሽ ወኪል ሆነው አገኛቸዋለሁ። ከሁሉም በላይ ደግሞ አበጀ በለው እንደ ፋኖ ትኩረቴን በእጅጉ ይሰበዋል።

በመጸሐፉ እንደ ተተረከው አበጀ በለው ሰላማዊ ኑሮውን ትቶ የሸፈተው በራሱ በደል ደርሶበት ወይም ወንጀል ሠርቶ ለመደበቅ ሳይሆን፤ ጎንቻ የፊታውራሪ ሽመልስ አሽከሮች የባላገር ከብቶችን ሰርቀው ሲያበቁ፤ በእነሱ ሀጢያት አንድ ተቆርቋሪ ወገን የሌለው ምስኪን ሰው ተፈልጎ፣ ባልሠራው ወንጀል ተከሶ እና ንብረቱ ተወርሶ ወህኒ ቤት ታስሮ እንደ ሞተ ሲሰማ፣ ለግፉኦን ተቆርቁሮ ባደረበት ብስጭት ነው። የአበጀን ታሪክ ሳቢና አስገራሚ የሚያደርገው ከዚያ ምስኪን ሰው ጋር የስጋ ዝምድና ሊኖረው ቀርቶ፤ ጭራሹኑ በወሬ ካልሆነ በቀር፣ በአካል የማያውቀው መሆኑ ነው። ነገር ግን፣ አበጀ በለው ከብቶቹ ከሸጠ በኋላ፣ ጠብ-መንጃ እና ጥይት ገዝቶ በመሸፈት፣ በዱር በገደሉ እየተዘዋወረ የምስኪን አገሬውን ሀብት ንብረት እየጠበቀ እና በዘረፋ ላይ የተሰማሩ ሽፍቶችን አድኖ እየገደለ ለሕዝብ ዘብ የቆመ ትልቅ ጀብደኛ ገፀ-ባህሪ ነው።

በዚህም አገረ ገዥዎች የሚጠሉትንና የሚፈሩትን ያህል፤ የአገሬው ሰው በፍቅር ወድቆ ያወድሰው፣ ይዘመርለት፣ ይዘፈንለት፣ ይሳሱለትና ይገዛለት ነበር፡ : ምክኒያቱም አበጀ የሕዝብ ልጅ ነውና። አበጀ በለው ከትውልድ ቦታው ጉልት እና እናሞራ ወደ፣ ጎንቻ እና ሳር ምድር ተጉዞእ በርካታ ፊታውራሪዎችን ድል አድርጎ ሰባት ዐመት ገዝቷል። ይህም ሆኖ፣ የጎንቻ ሕዝብ በጀግንነቱ ተማርኮ ወደ ትውልድ ቦታው ሲሄድ፣ እግሩ ላይ ወድቆ ለምኖታል። አበጀ ዘራፊና ተራ ሽፍታ አይደለም። ይልቁንስ በዝባዥ ገዥዎችን ለማስታገስ በግፍ ለሚሰቃይና ለተጠቃ ታጥቆ የተነሳ የማኀበረሰቡ ተቆርቋሪ ነው። በፊታውራሪ መሸሻ በሪሁን የአሽሙር አጠራር ደግ ሽፍታ ነው። ፊታውራሪ መሸሻ ከንቱ ሀገረ ገዥ ናቸው። ሰው ስትላቸው አፈር…፣ አዋቂ ስትላቸው ህጻን…፣ መላዕክ ስትላቸው ሰይጣን…፣ ጀግና ስትላቸው ወላዋይ…፣ ብርቱ ስትላቸው ደካማ…፣ ብልህ ስትላቸው ሞኝ…፣ ለጋስ ስትላቸው ራስ ወዳድ…፣ ዙፋን ስትላቸው አመድ… የሚሉ ሰው ናቸው። ብቻ ምን አለፋችሁ ላም እሳት ወልደች ዐይነት እየወደድኩ የጠላኃቸው ገፀ ባህሪ ናቸው። ይህም ሆኖ፣ የሚታዘንላቸው እንጂ፣ የሚታዘንባቸው አይደሉም። ፊታውራሪ በእውናቸውም በህልማቸውም አንድ የሚያውቁት ሙያ ቢኖር እንዋጋ ብቻ ነው።

Continue Reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*