ፍጻሜ ያጣ ሕልም | ግርማ ተ. ፋንታዬ

የሰሜኑ ጦርነት ተፋፍሞ አገር ምድሩ ጦር አዝማች የነበረ ሰሞን፣ አንድ ወዳጄ በዙሪያው የሚከናወነውን ጉድ ሁሉ ታዝቦ፣ የትኛውም ዜጋ ይሁን የበጎ ፈቃደኛ ስብስብ፣ በምድሩ ላይ የሚዘንበውን ክፉ እጣ ለማስቀረት እንደማይችል ሲታሰበው፣ “በዚህ ጦርነት የተረዳሁት ሁላችንም ምንም ነገር ለማድረግ ዐቅመ-ቢስ መሆናችንን ነው” ሲል ሰማሁት ዐዲስ ነገር እንዳገኘ ሁሉ።

ወዳጄ ያን ሰሞን ጠቆም እንዳደረገኝ፣ እንደ ሕዝብ ድምጻችን የማይሰማ ዐቅመ-ቢስ እንዴት ሆንን? ብዬ ማሰላሰል አልተውኩም። ድሮ ሁሉ ነገር የእግዜር ፈቃድ ነበር። ከ1966ቱ አብዮት ወዲህ ባለው ዘመን ግን፣ ባመዛኙ እንዲህ አይደለም። እግዜር ያን ያህል አይፈራም። የሃይማኖት ተቋማቱም በስሙ ገንዘብ ከማሰባሰባቸው በቀር፤ ከእኛ እንደ አንዱ እንደሆኑ እያየን ነው። በእግዜር ፈንታ፣ እጣችንን የሚወስንልን፣ እንደ አጥፊ ልጅ የሚቆጣጠረን የመንግሥት ሥርዐት ተዘርግቶልናል። በልጆቻችን እድል ላይ የሚወስኑልን፣ እንዳሻቸው አስረው የሚፈቱን፣ አዝምተውአዋግተውን ቁስላችን ሳይጠግግ፣ ወደ ቀጣዩ አጀንዳ ቢሻገሩ የኅሊናም ሆነ የአሠራር ተጠያቂነት የሌለባቸው “መንግሥት” በሚባለው የቢሮክራሲ መዋቅር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች እስረኛ ነን።

ከአራት ኪሎ እስከ ታችኛው አካል ያሉ ቢሮክራቶችን ‹እምቢ! አድቡ!!› ማለት በማንችልበት ሕዝባዊ ዐቅመ-ቢስነት ውስጥ ነን። ተጠያቂነት ሲያልፍም በማይነካቸው፣ ፍላጎታቸውን በሕዝብ ላይ እንዳሻቸው የሚጭኑ የመንግሥት ቢሮክራሲን የተቆጣጠሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች በሙሉ የፈለጉትን ሲያደርጉብን ኖረዋል። ‹ዛፍ ትከል› ሲሉ፣ መትከል፤ ‹ዝመት› ሲሉ፣ መዝመት፤ ‹ታጠቅ› ሲሉ፣ መታጠቅ ነው። ምናልባት ዋናው የችግራችን ምንጭ፡- በሥልጣን ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ኅሊና እንዲወቅሳቸው ወይ እግዜርን እንዲፈሩ ከመለማመን ውጪ፤ ለዚህ ተጠያቂነት የሌለበት ማን አለብኝነት ያበቃቸውን መዋቅራዊ መደላደል አለመጠየቃችን ነው። የሀገረ-መንግሥቱ የአስተዳደር መዋቅር “በዘመናዊ” መንገድ ማዕከላዊነቱ ጎልብቶ ከተቋቋመ ከሃያኛው መባቻ ጀምሮ፣ ጥቂት ግለሰቦች እና ስብስባቸው በኢትዮጵያውያን እጣ ላይ ፍላጎታቸውን ለመጫን የሚጠበቅባቸው፣ የሚከፈለውን ከፍለው የመንግሥትን ቢሮክራሲያ መቆጣጠር ብቻ እንደሆነ አይተናል።

ይህ ግዙፍ የመንግሥት የአስተዳደር ሥርዐት፣ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ሥልጣንን ከሕግ በታች እንዳያውሉ ቀፍድዶ በመያዝ፣ መላውን ሕዝብ የመንግሥት ጭሰኛ አድርጎታል። ቢሮክራሲው አገሪቱን ከድህነት አላወጣም። ትርፍ አምርቶ አያውቅም። የዜጎችን ደኅንነትም በአስተማማኝ አላረጋገጠም። ወደ ማማው የሚወጡ ጥቂት ስብስቦች በብዙሃኑ እድል ፈንታ ላይ የሚወስኑበት፣ ያሻቸውን የሚያቅዱበት፣ የፈለጉትን የሚያበለጽጉበት እና የሚያደኽዩበት ነው። በጀቱ፣ ሲቪል ሰርቪሱ፣ ጦሩ በጃቸው ነው። በአጭሩ፣ አስተዳደራዊ ዘይቤያቸው ተጠያቂነትን የሚጠየፍ እና ጦስ (ሪስክ) አሻጋሪ ነው።

Continue reading

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*