
ከሁለት ዐመታት ወዲህ በግልጽ መታየት የጀመረው የዐቢይ አህመድ መንግሥት እና የባይደኗ አሜሪካ ጠብ በዚህ ደረጃ ገሃድ ይወጣ ዘንድ የታሪክ ፍርድ ሆኗል። ትራምፕ የነካካውን፣ ባይደን አጨማልቆታል። የቀዝቃዛው ጦርነት ግብ-ግብ እንደ ዐዲስ ተወልውሎ ከች ብሏል። ጥቂት የአሰላለፍ ሽግሽግ ከመደረጉ በቀር፤ አጨዋወቱ ያው ነው። ቻይና ከፊት መጥታለች፤ ሩሲያም ሸንቀጥ ብላ ከኋላ ትንጎማላለች። የእኛ የዛሬ ፍልሚያ በዐቢይ፣ በኢሳያስ እና በፋርማጆ ሜዳ ይካሄዳል። መንግሥቱ፣ ኢሳያስ እና ዚያድ ባሬን አስታውስ። ጌታቸው ረዳ እና ድሪባ ኩምሳ (ድሪባ ኩማ ግን የት ሄዶ ነው?) አራጋቢዎች ናቸው። ከቀይ ባህር እስከ ላቲን አሜሪካ ከአውሮፓ እስከ ኢንዶ ቻይና፣ ከአፍጋኒስታን እስከ በርሊን… ካፒታሊዝም የጦር ክተቱን አውጇል።
ጌቶች “ኢንተርናሽናል ኦርደር፣ አሜሪካን ሄጅመኒ”… ምናምን ይሉታል። “ኮሚዩኒዝምን ለመክበብ ነው” የሚሉትም ነገር አላቸው። ወደ አራት ኪሎ ስናስጠጋው ደግሞ “ኩፒታሊዝም” ይሆናል። ሲአይኤ፣ የዐቢይ አህመድን መንግሥት በማንኛውም መንገድ ለመገልበጥ እየተፋለጠ ይመስላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሹማምንቶቻቸውን ሰብስበው፡- “እኛን ያስቸገረን የኦሎምፒያው ሲአይኤ ነው!” ይላሉ አሉ። ኦቦ ታዬ ፖስት የሚያደርጋትን ሽርደዳ እያሰበ ስለነበረ፣ የሰውዬውን ንግግር አልሰማም። ግድ የለም! ጨፌው ላይ “አካሄድ” ምናምን ካለ በኋላ ይሰማዋል። ‘ጻድቃን ገ/ተንሳአይ ሸዋሮቢት ደርሻለሁ” ይላል። በታሪክ የመጀመሪያው እስር ቤት ድረስ ሄዶ እጅ የሰጠ ወንጀለኛ ለመሆን ይመስላል። “ጦርነቱ አልቆ ምኑን ነው የምንደራደረው?!” ይልሃል ሲያሻው። ፖለቲካ ትንሽ ቢሆን፣ ሳይንስ ይመስለኝ ነበር።
እናልህ አንባቢዬ! የሲአይኤ ወሮ በሎች በቦሌ ጎዳናዎች ላይ እየተቅበዘበዙ ነው። “መንግሥቱ ኃይለማርያምም ሊሄድ ሲል እንዲህ ነበር” እያሉን ነው። እስከ አሁን ያቆዩት ፈልገው አይመስልም? ከእናንተ የሽሮሜዳ ‘ኮምፕሌክስ’፣ የስካይ ላይት ሆቴል ተሻለ እኮ። ዝርዝሩን ወርቁ ጋቸና ያብራራልህ። በኮክቴል ጋዜጠኞች ወሬ የመንግሥትን እጣ ፈንታ መተንበይ ድሮ ቀረ። ያቋረጣችሁት የሴኪዩሪቲ ፈንድ ትዝታ ብቻ ተመዝግቦ ይቆየን። እና መንጌ ሲሄድ ብቻም ሳይሆን፤ “ሲመጣም፣ ሲከርምም ከዚህ ይብስ ነበር” እያልኩህ ነው። “ደርቲ ትሪክስ” የሚሉት ሴራ አላቸው። የማይፈልጉትን መንግሥት ለመገልበጥ የሚሄዱባቸውን ርቀቶች የሚገልጽ ስያሜ ነው። የታሪክ ሰነዶቻቸው በግልጽ ይመሰክራሉ።
Be the first to comment