
በድሬዳዋ ከተማ በተፈጠረው የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎች መጉላላታቸውን ገለጹ። በተፈጠረው የቤንዚን እጥረት ሳቢያ በከተማ ነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም ሰልፎችና አላስፈላጊ የጊዜ ብክነት መከሰቱን የድሬዳዋ ከተማ የባጃጅና የታክሲ አሽከርካሪዎች ቅሬታቸውን ተናግረዋል።
በተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ሳቢያ የታክሲ ተገልጋዮች ላይ አላስፈላጊ ጭማሪ ለማድረግ መገደዳቸውን ሀሳባቸውን ለመገናኛ ብዙሃን የሰጡ የታክሲ አሽከርካሪዎች ተናግረዋል። መንግስትም የሚታየውን እጥረት በመፍታት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ችግር እንዲቀርፍ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። ነዳጅ ማደያዎችም አቅርቦቱን ፍትሃዊ በመሆነ መንገድ እንዲያከፋፍሉ የሚመለከተው አካል ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበትም አውስተዋል።
በየወሩ መጨረሻ ላይ ከ23 እስከ 30 ባሉት ቀናት የነዳጅ ዋጋ ላይ ጥቁር ገበያ አለ የሚሉት አሽከርካሪዎች፤ በዚህ መንገድ በሚሸጠው ነዳጅ ከመደበኛ ዋጋ በላይ እንደሆነም እማኞች በተለይ ለፍትህ መጽሔት ተናግረዋል። ነዳጅ ማደያ ያላቸው ባለሀብቶች ሶስት ቦቴ (ተሳቢ) ለማከፋፈል ይረከቡ እና አንዱን ቦቴ በማስቀረት የአየር በአየር ንግድ እንደሚያካሂዱ ይናገራሉ።
ወደ ከተማዋ ከሚገቡት ውስጥ አንደኛው ነዳጅ የጫነ መኪና ለባለ ሶስት እግር (ባጃጅ) ላይ እንዲቀዳ ይደረጋል። በመቀጠል ከባጃጆች በችርቻሮ በማስቀዳት ለሶስት ሊትር እስከ ሶስት መቶ ብር እንደሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎች ይናገራሉ። ለአንድ ሊትር ቤንዚን በአማካይ ከ18 -22 ብር የሚሸጥ ነዳጅ በጥቁር ገበያ ሶስት ሊትር ከአስር እጥፍ በላይ እንደሚጠየቅ ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል።
ነዳጅ ለመቅዳት ሌሊት 10፡00 ወረፋ የያዙ ባለመኪናዎች ተራ የሚደርሳቸው ጠዋት ሁለት ሰዓት እንደሆነ ይናገራሉ። በዚህ የተነሳ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ተጨማሪ ክፍያ እንደሚጠየቁ የሚናገሩት እማኞች፤ እንደምክንያት የሚሰጠው የነዳጅ እጥረት እንደሆነ አሽከርካሪዎች ይናገራሉ።
በጉዳዩ ላይ የኃላፊዎች እጅ እንዳለበት የሚጠረጥሩት ሾፌሮቹ ችግሩ እንዳይቀረፍ ምክንያት የሆነውም ይሄ ነው ባይ ናቸው። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የክልሉ የዜና ወኪል የሚመለከታቸውን ሐላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን በዘገባው አስታውሷል።
ኑሮ ድሬዳዋ በጣም ከባድ እንደሆነ የሚገልፁት ነዋሪዎች ከከተማዋ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ የረር ከሚባል ሰፊ የአትክልት እርሻ የሚመጣ አትክልት ከተማ ላይ በሶስት እጥፍ ዋጋ እንደሚሸጥ ያስረዳሉ።
ሆኖም በየረር አካባቢ ግን ዋጋው ቅናሽ ነው መሆኑን ነግረውናል። በአንፃሩ ስኳር ደግሞ በኪሎ እስከ ሀምሳ ብር እየተሸጠ እንደሚገኝም ገልፀዋል። በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ውስጥ እንደሚገኙ የሚገልፁት የከተማዋ ነዋሪዎች የክልሉ መንግስት እና ፌዴራል መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲሰጣቸውም ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
በርካታ የስራ አጥ ቁጥር ይገኝባታል የምትባለዋ ድሬዳዋ ተመሳሳይ የስራ እና የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሰራተኞችን እኩል አታስተናግድም። የስራ እድል የሚያገኙት በብሄራቸው እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይላሉ ነዋሪዎች።
ኮንትሮባንድ እና ድሬዳዋ
በተያያዘ የከተማዋ ዜና ኮንትሮባንድ እቃዎች ወደ አካባቢያቸው ከሚያስገቡት ውስጥ ድሬዳዋ አንዷ እንደሆነች የጉምሩክ ባለስልጣን ይፋ ያደረገው መረጃ ይጠቁማል።
ኮንትሮባንድ እቃዎች በተጨማሪም የውጪ ሀገራት ገንዘቦች ወደ ከተማዋ እንደሚገባ በተደረገው ክትትል ማወቅ ተችሏል። ባለፉት 5 ቀናት ውስጥ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ብቻ 31 ሚሊየን 614 ሺህ 620 ብር የሚገመት ወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣብያዎችና ኬላዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገቢዎች ሚኒስትር አስታውቋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችም የተለያዩ አደዲስና አሮጌ አልባሳት፤ የአይን መነጽሮች፤ ኤሌክትሮኒክስ፤ ጊዜ ያለፈባቸው ምግቦች፤ የሴቶች መዋቢያ ፓውደሮች፤ የተለያዩ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች፣ ጄነረተሮች፣ ሀይል አባካኝ አምፓሎች፤ የዝሆን ጥርስ፤ የአዋቂና የልጆች ጫማዎች፤ የምግብ ዘይት፤ ለስላሳ መጠጦች፤ ሽቶዎች፣ የተለያዩ ተሸካርካሪዎች፤ አደንዛዥ ዕፅ (ሀሺሽ) እና ሌሎች እቃዎች ሲሆኑ ከላይ በብሎኬት በመሸፋንና በተሸከርካሪ ኪስ ውስጥ በመደበቅ ለማሳለፍ ሲሞክሩ ተይዘው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።
በነዳጅ ዋጋ እና በኑሮ ውድነት እንዲሁም በበርካታ በስራ አጥ ቁጥር የምትዳክረው ድሬዳዋ የኮንትእሮባንድ ንግድ እየናጣት ይገኛል። አዲሱ የብልፅግና ፓርቲ በሚሰጠው ስልጠና ላይ የከረሙት የድሬዳዋ ከፍተኛ ባለስልጣናት በከተማዋ የሚታዩትን ችግሮች ይፈቱ ይሆን የሚለው ጥያቄ ሁሉም የሚያነሳው ነው።
Be the first to comment