የመተከል ውጥረት

ተከል ዞን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገኛ ከመሆኑ አኳያ የተፋሰሱ አገራት የተለየ ትኩረት አድርገውበታል። አካባቢውን የልማት ሳይሆን የግጭት ማዕከል ለማድረግ ብዙ እየሰሩ ነው ማለት ይቻላል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ‹በይገባኛል› በሚወዛገቡባቸው የድንበር ጉዳዮች፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች መልሰው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደሚያስነሱ ሱዳን ማስጠንቀቋ ይታወሳል። የሱዳን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ የሁለቱ አገሮች ልዩነት በግድቡም ሆነ በድንበር ውዝግባቸው መበርታቱን የሚጠቁም የከረረ ትችት በኢትዮጵያ ላይ ሰንዝሯል።

ሱዳን፣ ‹ኢትዮጵያን በዓባይ ውሃ እና በድንበር ጉዳዮች ላይ ከተፈረሙ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ለማቆራኘት እየሰራች ነው› እያሉ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሚሰጧቸውን መግለጫዎች በጥልቅ ሀዘኔታ እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል። “አገራት እና መንግሥታት በቀደሙ አገዛዞች እና መንግሥታት ለተፈረሙ ስምምነቶች እና ውሎች ቁርጠኛ መሆናቸው በዓለም አቀፍ ግንኙነት መሠረት የጣለ ልማድ ነው” ብሏል፣ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ መግለጫ። “ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ውሎችን፤ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን በማውጣት፣ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል እነርሱን የሚቃረን የሕዝብ አስተያየት በማደራጀት ገሸሽ ማድረግ፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን የሚበክል፣ ለአንድ ወገን ፍላጎት ተጋላጭ የሚያደርግ፣ ቀውስን የሚያስፋፋ፣ የጥሩ ጉርብትና መሠረትን የሚያናጋ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው” ሲል የከረረ ተቃውሞ ሰንዝሯል።

ስምምነቶች ሲፈረሙ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ሱዳን በአንፃሩ ቅኝ ተገዢ እንደነበረች በመግለጫው የጠቀሰው የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተናጠል የትኞቹ ስምምነቶች እንደሆኑ ማብራሪያ አልሰጠም። “ለፕሮፓጋንዳ እና ለአገር ውስጥ የፖለቲካ ምክንያቶች እንዲህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እየመረጡ ውድቅ ማድረግ በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ካለው ስምምነት ለመድረስ የማይረዳ ጎጂ እና ዋጋ የሚያስከፍል እንደሆነ ለማሳሰብ እንወዳለን” ብሏል።

Continue reading

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*