አብዮት የሸተታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር | አበበ አካሉ ክብረት

የዛሬ ጽሑፌን “ሄጌ ማሲናኒ፣ ቄሴ ዲገናኒ፣ ቡሺሮ ዲአጉራኒ! (መቼስ ምን ይደረጋል? ቄስ አይመታም፤ መጥፎ ከሆነ ወይም ካስቸገረ ግን አይተውም!”) በሚለው የሲዳምኛ አባባል እጀምራለሁ።

ከዓለማችንም ሆነ ከአገራችን የቅርብ ዘመናት ታሪክ እንደምንረዳው፣ አብዮት ሕዝብ ባልተመቸውና ባልፈለገው አገዛዝ ላይ “እምቢኝ!” ብሎ ለውጥ ለማዋለድ የሚያምጽበት ክስተት ነው። ሕዝብ ያስከፋውን ሥርዐት ሽሮ ሌላ ለመተካት ያምጻል። በተለይ በየጊዜው ለሚነሱ ፈርጀብዙ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዳተኛ የሆነ፣ ብሶትን የማያዳምጥ፣ ከታች እስከ ላይ በዘረጋው መንግሥታዊ የአስተዳደር መዋቅር የሚፈጸመው በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሄዶ የግፍ ጽዋው ሲሞላ… ሕዝባዊ እምቢተኝነት እውን ይሆናል።

ወደ አገራችንም ብንመጣ፣ በወቅቱ እንደ መለኮታዊ ኃይል የሚታየው የዘውድ አገዛዝን ለረጅም ዐመታት የተሸከመው ሕዝብ፣ በመጨረሻም ባዋለደው አብዮት መገርሰሱ የግማሽ ክፍል ዘመን ታሪክ ነው። እንደሚታወሰው፣ በኢትዮጵያ ለ1966ቱ አብዮት መከሰት መሠረታዊ ጉዳይ የነበረው ለዘመናት ሲጠራቀም የመጣው ግፍና ጭቆና ነው። በርግጥም፣ የሰው ልጅ አድፋጭ እንጂ፣ እስከ ወዲያኛው በተሸናፊነት አንገቱን ደፍቶ የሚኖር ባለመሆኑ፤ እጅ እጅ ያለውን አገዛዝ ከጫንቃው ላይ አሽቀንጥሮ የሚጥል የአብዮት ጎዳናን ለመምረጥ መገደዱ ተፈጥሯዊ ነው። ነገር ግን፣ በየትኛውም አገር የፖለቲካ ሂደት የሥልጣን ሽግግሩ በሕዝብ ድምጽ ሲጸና መሰልጠንን ያሳያል፤ አገርን ለቀጣይ ትውልድ ያሻግራል፤ ፍትሐዊነትንም ያሰፍናል። ይሁንና ለዚህ ዐይነቱ ክስተት ገቢራዊነት ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው። በተለይ የሕዝቡን የየዕለት እንቅስቃሴና ፍላጎት መመዘን የማይችል እና ለሚነሱ ጥያቄዎች ጆሮ ዳባ ልበስ የሚል መሆኑን ጨምሮ፤ ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ ሲያጣ ወደ ዐደባባይ ገንፍሎ በመውጣት ማመጹ አይቀሬ ነው። ይህን መሰሉ ሕዝባዊ ዐመጽ ጊዜውን የማይዋጅና ፍጽሞ አላስፈላጊ ቢሆንም፤ ድንገት እንደሚገነፍል የጀበና ቡና አንዴ “ቡፍ” ካለ በቀዝቃዛ ውሃ አይመለስም። የጀበናው አፍ ዙፋን ላይ እንደ ጉልላት የተቀመጠውን ክዳን አሽቀንጥሮ ያፈርጠዋል።

ነፍሳቸውን ይማረውና፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊም ሆኑ ፓርቲያቸው የአብዮት ፍራቻቸው ወደር-የለሽ እንደነበረ አስታውሳለሁ። በተለይ የዐረብ ስፕሪንግ መስቀል ዐደባባይን እንዳይጎበኝ አቅጣጫ ለማስቀየር ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ዛሬ ለአገራችን እጅግ የገዘፈ ጠቀሜታ ያለው የህዳሴው ግድብ ሳይቀር የተጸነስው ከማስቀየሻ ካርዶች አንዱ ይሆን ዘንድ በመታጨቱ ነበር። መቼም፣ በወቅቱ የቀለም አብዮት ተንታኝ ካድሬዎች እንደ ጉድ በዝተው እንደነበረም አይዘነጋም። ግና፣ አቶ መለስ በህይወት ቆይተው በዓይናቸው ባይዩትም፤ ከደደቢት እስከ አራት ኪሎ ተዋድቀው የመሰረቱት መንግሥት ፍፃሜ፣ እሳቸው እንደፈሩት በአብዮት መበላት ከመሆን የታደገው የለም። የአሁኖቹ ደግሞ፣ ሕዝባዊ ብሶት የሚያዋልደው Revolution የመነሳቱን እድል፣ “ሬቮ” መኪና የመግዛት ያህል አቅልለው የተመለከቱት ይመስላል። የሆነው ሆኖ፣ በየትኛውም መስፈርት ለመንግሥታዊ ሥርዐት ለውጥ አብዮት አይመከርም።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*