የመንግሥት ፌዝና የምክክር ኮሚሽኑ ሚና | ዶ/ር ሔሮን ገዛኽኝ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)

የብሔራዊ ምክክር ጽንሰ-ሃሳብ እ.ኤ.አ ከ2013 እስከ 2014ት ከተደረገው የየመኑ National Dialogue ወዲህ ነው፣ ዓለም ዐቀፍ ትኩረት እያገኘ የመጣው። ይህም ሆኖ፣ ምግባራቸው ብዙም ከብሔራዊ ምክክር የማይለይ፣ ሌላ ስያሜ የተሰጣቸው መሰል ኩነቶች ይከናወኑ እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። የዘርፉ ባለሙያዎችም የ1787ቱን የአሜሪካ ሁሉን ዐቀፍ ሕገ-መንግሥት የመቅረጽ የድርድር ሂደትን በዋቢነት ይጠቅሳሉ። በአንድ አንድ የደቡብ አውሮጳ እና ምስራቅ እስያ አገራት ደግሞ፣ በ1970 እና በ1980ዎቹ የተደረጉ የፖለቲካ ሪፎርሞች፣ የሽግግር ሂደቶችና ሕገ-መንግሥት

የመቅረጽ እንቅስቃሴዎች ከብሔራዊ ውይይት ጽንሰ-ሃሳብ ጋር ተመሳስለው ሲቀርቡ እናያለን። በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ በፖለቲከኞች፣ በምሁራን እና በሲቪክ ማኀበራት መካከል “Global South” በመባል በሚታወቁት አገራት የተደረጉ ፍኖተ-ካርታ የመቅረጽ ድርድሮችም፣ ከብሔራዊ ምክክር ጋር ተመሳሳይነት አላቸው።

በጥቅሉ፣ በታሪክ የተመዘገቡና በአጠረ ጊዜ የተጠናቀቁ ብዙዎቹ ብሔራዊ ምክክሮች፣ በልሂቃን መካከል የጋራ ስምምነትን መፍጠር ስለመቻላቸው ይነገራል። ስምምነቶችን በወጉ በመተግበር ረገድ ግን፣ ግማሽ ያህሉ እንኳ ውጤታማ ሳይሆኑ እንደቀሩ ጥናቶች ያስረግጣሉ።

የሆነው ሆኖ፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የተርታው ሕዝብ፣ የሲቪክ ማኀበራት፣ የምሁራን እና የሌሎች ቀጠናዊም ሆነ ዓለም ዐቀፋዊ ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ፣ ለውጤታማ ብሔራዊ ምክክር መሰረት መሆኑ ይታወቃል። ለዚህ ደግሞ፣ የዳበረ የንግግር ባህልና ልምድ፣ እንዲሁም የተረጋጋ አገራዊ የጸጥታ ሁኔታ መኖሩ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው። በሌላ በኩል፣ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ውክልና፣ ሂደቱን የሚመራ ተቋም ተአማኒነት፣ የኃላፊዎቹ ገለልተኝነት፣ ለድርድሩ የሚደረገው ጠንካራ መንግሥታዊ እና ሕዝባዊ ድጋፍ፣ የሚዲያዎች ተሳትፎ እና አጠቃላይ ሂደቱ የሚወስደው ጊዜ… ለአንድ ብሔራዊ ምክክር ፍሬያማነት ቁልፍ ሚናን  እንደሚጫወት አጽንኦት ይሰጥበታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ ወጥኖ ሂደቱን የሚመራ ኮሚሽን በአዋጅ ማቋቋም ከጀመረ መሰንበቱ ይታወቃል። ተቋሙን የሚመሩ 11 ኮሚሽነሮችንም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርጦ ይፋ አድርጓል። እነዚህ ተመራጭ ኮሚሽነሮች ምክር ቤቱ ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች በማሟላት በሕዝብ ከተጠቆሙ 632 ዕጩዎች መካከል እንደተመረጡም ተነግሯል። ይሁንና፣ ሂደቱ በብዙ የፖለቲካ ተዋንያን እምነት ሳያገኝ ቀርቷል። በተለይ ለምርጫ የተሰናዱት መስፈርቶች ግልጽነትና ተጨባጭነት የጎደላቸው ከመሆናቸው በላይ፤ የሁሉም ተጠቋሚዎች ማንነት በይፋ አለመገለጹ ብዙዎችን ቅር አሰኝቷል። …

Continue reading

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*