ጎንደር ለምን የግጭት ማዕከል ሆነች? | ጌታቸው ሽፈራው

ከቅርብ ዐመታት ወዲህ፣ በተቀደሰው የረመዳን ወር ሰላማዊውን ሙስሊም ተገን አድርገው እየተፈፀሙ ያሉ ችግሮችን፣ ለማጋለጥ የቻልነውን ይህል እየሞከርን ነው። ከዚህ ልምድና ከሌሎች ምልክቶች በመነሳት፣ የዘንድሮውም ቢብስ እንጂ፣ የተሻለ ሆኖ ስላልታየኝ፤ የረመዳን ፆም ከመግባቱ ጥቂት ቀናት በፊት፣ የአክራሪዎችን አካሄድ በደንብ ለሚረዱ ሁለት ጓደኞቼ ስልክ ደውዬ፣ ‹በረመዳን ወቅት ሊፈጠሩ ይችላሉ› ብዬ የሰጋኋቸውን ጉዳዮች ካጋራኋቸው በኋላ፤ “ሴራቸውን ለማክሸፍ ቀድመን ስለጉዳዩ በመጻፍ ሕዝብ እንዲያውቅ አድርገን ብናጋልጣቸው ጥሩ አይደለም ወይ?” ብዬ አማክሬያቸው ነበር። ነገር ግን፣ ሁለቱም ሀሳቤን ተቃወሙት። ለሌሎች ሰዎችም ይህንኑ ስጋቴን አጋራሁ። ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ቻግኒ፣ ሞጣ፣ እንፍራንዝ፣ ኮምቦልቻ፣ ከሚሴ፣ እስቴን… እየጠቀስኩ በፌስቡክ ስዘረዝራቸው በነበሩት ቦታዎች ላይ ያረበበውን ስጋት አስረዳዋቸው። አንዳንዶቹ ‹ጻፈውና ለመንግሥት አካላት እናድርሰዋለን፣› ብለውኝ ስላደፋፈሩኝ፣ ጽፌው ለመንግሥት እንዲደርስ ተደርገ።

ይህ ስጋት እንዲሁ ከሜዳ የመጣ አይደለም። ከጥቂት ዐመት ጀምሮ በእምነት ስም የሚደረጉ ትንኮሳዎች አዋጭ የግጭት መነሾ እየሆኑ ነው። በተለይ በረመዳን ወቅት የተሰገዱባቸው ቦታዎችን ድንጋይ በመኮልኮል ‹የእኛ ናቸው› በሚል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሠሩ መኖራቸው ተስተውለዋል። በጎዳና ላይ አፍጥርና በሌሎች አጀንዳዎች የተጠመዱ አካላትም፣ ከፌደራል መጅሊስ ጋር ያላቸውን ልዩነት ግጭት በመፍጠር ለመፍታት፣ የሙስሊም አባቶችን ጭምር እረፍት ነስተው መቆየታቸው ይታወቃል።

እንደገና ያገረሸው የእምነት ልዩነት

የድምፃችን ይሰማ ንቅናቄ “መንግሥት አህበሽን በግድ ጭኖብናል፣” የሚለው ዋንኛው ጥያቄ፣ የሕዝብ- ሙስሊሙን መሪዎች ለሁለት የከፈለ እንደነበረ ይታወሳል። ይህ ጉዳዩ ባለፉት ዐመታት በእርቅና በውይይት ባለመፈታቱ፣ ዘንድሮ ጠንካራ ቃላት ወደማወራወር ተሸጋግሯል። ሆኖም ግን፣ የተፈጠረውን ልዩነት፣ አንደኛው ቡድን የመጅሊስ ጥያቄ አስመስሎ ሲያጎነው፤ “አህበሽ” እየተባሉ የሚወገዙት ደግሞ በግልጽ “ልዩነታችን የነባሩ ሙስሊም እና የወሃቢያ ጉዳይ ነው” ከማለትም አልፈው፤ ያኛውን ቡድን በጽንፈኝነት ይወነጅሉታል።

ካለፈው ዐመት ጀምሮም ሀጅ ሙፍቲ ይህን ጉዳይ በተመለከተ፡- “ነባሩ ሙስሊም እየተገፋ ነው፣ አባቶች ከፍተኛ ወከባ እየደረሰባቸው ነው፣” ብለው በዐደባባይ በተደጋጋሚ ሲናገሩ መደመጡን ያዙልኝ። በጽንፈኛው ቡድን ሲወገዝ የኖረው ኡስታዝ ሀሰን ታጁም ከአንድ ወር በፊት “ሀሪማ” በተሰኘ ሚዲያ፣ የወሃቢ/ሰለፊ አደጋነትን እና ነባሩ ሙስሊም ላይ እያደረሰ ያለውን ወከባ በሦስት ክፍል አብራርቷል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድም፣ “የሙስሊሙን ጉዳይ ለመፍታት” በሚል ያቋቋሙትን ኮሚቴ፣ ከነባሩም ከወሃቢያውም በተወከሉ ሰዎች አመጣጥነው ማዋቀራቸውን ሀሰን ታጁ በቃለ-መጠይቁ ጠቅሶታል።

በተቃራኒው፣ የወሃቢያው ቡድን መሪዎች የአስተምህሮ ልዩነት መኖሩን ለመናገር አይፈልጉም። ወሃቢያ/ሰለፊ እና ሱፊ ተባብለው ከተነጣጠሉ፣ በአባቶች ተቃባይነትን እንደማያገኙ ስለሚያውቁት አጀንዳውን፡- የሙስና፣ የመልካም አስተዳደርና የመጅሊስ ጥያቄ አድርገው ያድበሰብሱታል። ለዚህም ነው፣ ቡድኑ ልዩነቱን በይፋ ከመናገር ይልቅ፤ በዐደባባይ የለውጥ ንቅናቄ መሪ መስሎ በመታየትና ግጭት በመፍጠር በወጣቱ ዘንድ ድጋፍ ለማግኘት ሲጥር የሚስተዋለው።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*