
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የነበሩት ዶ/ር ሙሉ ነጋ ከኃላፊነታቸው ተነስተው በምትካቸው ዶ/ር አብርሃም በላይ ተሹመዋል። የሀላፊነት ሽግሽግ የተደረገው ቀድሞም ካቢኔው የተቋቋመው የጊዜያዊ አስተዳደር ስለነበር ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለፍትሕ መጽሔት የሰጡት ዶ/ር ሙሉ ነጋ፣ እየተሰጡ ያሉት አሉታዊ አስተያየቶች ከእውነት የራቁ ናቸው ሲሉም አስተባብለዋል።
የኃላፊነት ሽግሽጉ የተደረገው በቅርቡ በተካሄደው የስብሰባ ነበር ያሉት ዶ/ር ሙሉ፣ ላለፉት ስድስት ወራት ክልሉን በማስተዳደር ላይ እንደነበሩና ጥሩ አፈጻጸም እንደነበራቸውም ነግረውናል። ምናልባትም ሌሎች በክልሉ ሀላፊነት ላይ ያሉ ሰዎችም ወደ ሌላ ሀላፊነት ሊዘዋወሩ እንደሚችሉም ጠቁመዋል። ክልሉ በአንጻራዊነት መረጋጋት እንደሚታይበትም ጨምረው ገልጸዋል።
የህወሓት ደጋፊዎች በበኩላቸው፣ ዋና አስተዳዳሪው የተነሱት ኃፊነታቸውን በሚገባ ስላልተወጡ ነው ይላሉ። አያይዘውም የፌዴራል መንግስትን ተልእኮ ማስፈጸም እንጂ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በራሱ የሚወስነውም ሆነ የሚያከናውነው ተግባር የለም በሚል ትችት ያነሳሉ። ሆኖም ዶ/ር ሙሉ በእነዚህ አስተያየቶች እንደማይስማሙ ይገራሉ። ክልሉን በማቋቋም ደረጃ ከፌዴራል መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ እንደሆነ በመግለጽ፣ ምንም ኃላፊነት የላቸውም፤ ትግራይን የሚያስተዳድረው አካል ሌላ ነው በሚለው ሀሳብ ግን ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ ለፍትህ መጽሔት ገልጸዋል።
Be the first to comment