ሰሚ ያጡት ንጹሃን ዜጎች

ኦሮሚያ ክልል አሁንም ለሌላ ክልል ተወላጆች ምቹ ከመሆን ይልቅ የሞት ቀጠና መሆኑን ቀጥሏል። በተለይ የአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ስቃይ ከእለት እለት እየጨመረ እንጂ ሲቀንስ አይስተዋልም። ለዚህም ክልሉን ከሚመሩት ከከፍተኛ ባለስልጣናት አንስቶ እስከ ጸጥታ መዋቅሩ ድረስ የዘለቀ ተጠያቂነት ሲነሳ ይስተዋላል።

ሁለተኛ ሳምቱን በያዘው የ‹‹ሆሮ ጉድሩ›› ጥቃትም፣ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፈጨፋ አሁንም መቀጠሉን የአካባቢው ነዋሪዎች እየተናገሩ ይገኛሉ። በመጀመሪያ ከደረሰው እና ፍትሕ መጽሔትን ጨምሮ በርካታ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት ያለፈው ሳምንት ጭፍጨፋ ከሃምሳ የሚበልጡ ንጹሃን ዜጎች በታጣቂው ኦነግ ሸኔ መገደላቸው ይታወሳል።

አሁንም ግድያውና መፈናቀሉ እንደቀጠለ ነው የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎቹ፣ ራሳቸውን መከላከል እንዳልቻሉና የክልሉ ልዩ ሀይልም ጥበቃ እንደማያደርግላቸው ይናገራሉ። በአካባቢው የሚገኘው ጥቂት ሚሊሻ ደርሶ ባያስጥላቸው ኖሮም ተጨማሪ የሰዎች እልቂት ይከተል እንደነበር ጠቁመዋል። የክልሉ ፖሊስ ህብረተሰቡን ከመጠበቅ ይልቅ ከታጣቂዎች ጋር በመወገን ለጥቃት እንደሚያጋልጣቸውም ተናግረዋል።

ከፌዴራል መንግስት ካልሆነ በስተቀር፣ ‹‹የክልሉ ሀላፊዎች መፍትሔ ይሰጡናል ብለን አናምንም›› ሲሉም ተደምጠዋል። ምክንያታቸውን ሲያቀርቡም፣ ከታጣቂው ቡድን ህይወታቸውን ለማትረፍ የሚሸሹትን በመመለስ ‹‹እኛን ታስወቅሱናላችሁ፣ ስማችንንም ታስጠፉታላችሁ›› በማለት እንደሚከለክሏቸው አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ እስካሁን በተደረገው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ስልሳ የሚደርሱ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ በርካቶችን ከቀጠፈው እና ከሳምንት በፊት ከተደረገው ጭፍጨፋ በኋም ሰባት ተጨማሪ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል። አሁንም የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው ጨምረው ጠቁመዋል።

ለሁለተኛ ጊዜ በታጣቂው የኦነግ ሸኔ ተከበው እንደነበር የሚናገሩት እነዚሁ ለደህንነታቸው የሚሰጉ ዜጎች፣ ከዚህ ቀደም ራሱን ለመከላከል እንዲችል የተደራጀው ሚሊሻ እንደታደጋቸው ጠቁመዋል። ሆኖም በአካባቢው የሚገኙት የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሀይሎች ሚሊሻዎቹን ወደከተማ በመጥራት ህዝቡን ለአደጋ እያጋለጡት እንደሆነ ተናግረዋል። ‹‹ለዚህም ነው ማዕከላዊ መንግስት ይታደገን ያልነው›› በማለት የአካባቢው የጸጥታ መዋቅር ጥያቄ ውስጥ የከተቱበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

ይሄን በመመልከት የክልሉ የጸጥታ አካላትም ሆኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ለህብረተሰቡ ግድ እንደሌላቸው ይናገራሉ። ምናልባትም በዚህ ጥቃት ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተሳታፊም እንደሚሆኑ ጥርጣሪያቸውን ያስቀምጣሉ።

አያይዘውም ከሆሮ ጉድሩ ውጪም በሌሎች አካባቢዎች ሰዎች እየታገቱ እንደሚወሰዱና እንደሚገደሉ መረጃ እንደሚደርሳቸው እየገለጹ ይገኛሉ። ‹‹ህዝቡ ወደ አማራ ክልልም ሆነ ወደ ሌሎች አጎራባች ስፍራዎች መሸሽ አልቻለም›› የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ዜጎች ራሳቸውን ለማዳን ንብረታቸውን እየተውና የደረሰ ሰብልም ሳይሰበስቡ እንደሚሰደዱ ተናግረዋል።

በአካባቢው የተፈጠረው ችግር አምስት ወራት በላይ ቢያቆጥርም፣ እስካሁን አንድም የመንግስት አካል መጥቶ እንዳላነጋገራቸው አሊያም የጎበኛቸው እንደሌለ አስታውቀዋል። ለጥቃት የተጋለጠውን ህብረተሰብ ከመጠበቅ ይልቅ በከተማ አካባቢ የሚገኙት ልዩ ሀይል አባላት፣ ችግር ተፈጥሯል ሲባል ብቻ እንደሚመጡ ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተጨማሪም የአካባቢው መውጫና መገግቢያ ላይ ሳይቀር የጸጥታ አካላት እንደሌሉ ይገለጻል።

በዚህ ምክንያት ዜጎች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ራሳቸውን ለመጠበቅና ለመከላከል ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በአንድ በኩል ራሳችሁን ተከላከሉ የሚባሉት እነዚህ ዜጎች፣ የሚመጣውን ጥቃት ለመከላከል ተሰብስበው መነጋገር ሲጀምሩ ‹‹ለምን ተሰበሰባችሁ›› ተብለው እንደሚታሰሩ ይናገራሉ።

ይሄን ሁሉ ግፍ የሚቀበሉት እነዚህ ዜጎች ‹‹ያለን አማራጭ ቁጭ ብለን ሲጨርሱን መጠበቅ ነው›› ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀርባሉ። ከኦሮሚያ ክልል የጸጥታ አካላት ይልቅ የፌደራል ፖሊስ አሊያም የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ቢገባ የተሻለ ጸጥታ እንደሚሰፍን እምነት ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ተስፋቸው በፌደራል መንግስት እንጂ በክልሉ ባለስልጣናት እንዳልሆነም አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለጥቃት የተጋለጡትን የህብረተሰብ ክፍሎች ‹‹ራሳቸውን እንዲከላከሉ እያጠናከረኩኝ ነው፤ ድጋፍም እየተደረገላቸው ነው›› ሲል የሚያቀርበውን ሀሳብ ነዋሪዎቹ አይስማሙበትም። ይልቁንም የእኛን መሳሪያ በመንጠቅ ለአደጋ እየዳረጉን ነው በማለት አስተያየቱን ያስተባብላሉ። አስከትለውም፣ ህብረሰተቡን ማደራጀትና ማጠናከር ቀርቶ፣ ‹‹የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በዚህ አካባቢ ይገኛሉ›› የሚለውን ጥቆማ ተከታትለው እርምጃ ለመውሰድ ፍቃደኞች አለመሆናቸውን በተደጋጋሚ መታዘባቸውን ያስረዳሉ።

ከህብረተሰቡ በተጨማሪ የአካባቢውን ሚሊሻዎች ‹‹ለምን ኦነግ ሸኔ ላይ እርምጃ ወሰዳችሁ›› ተብለው በልዩ ሀይል ተኩስ ተከፍቶባቸው እንደነበርም አስታውሰው፣ በኋላ ላይ አርባ የሚሆኑ የሚሊሻ አባላት እምዲታስርሰሩ ተደርገዋል ብለዋል። አንዳንዴም ሚሊሻው መሳሪያውን ለልዩ ሀይል ካላስረከበ እንደሚታሰር ማስፈራሪያዎች እንደሚነገሩ አስታውቀዋል።

በሆሮጉድሩ የሚገኙት እነዚህ ዜጎች፣ ጉዳይ የተወሳሰበ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ህዝቡ ሰብአዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብቱ እየተከበረ እንደማይገኝ ይናገራሉ። መፍትሄው ከፌዴራል መንግስት የሚመጣ ካልሆነ በስተቀር ሌላ አማራጭ እንደሌለም ያብራራሉ።

የተፈናቀሉት ዜጎች ወደሌሎች ወረዳዎች በመሄድና ያልተፈናቀሉትን የአማራ ተወላጆች ጋር በመጠጋት እርስ በርስ እየተደጋገፉ ይገኛሉ እንጂ ሌላ የሚግዛቸውም ሆነ የሚረዳቸው አካል እንደሌለ የአይን እማኞች ጠቁመዋል። ከተፈናቀሉት ውስጥ ህጻናት፣ አዛውንትና ሴቶች እንደሚገኙበተም ገልጸዋል።

እነዚህ በችግር ላይ ያሉ ዜጎች ራሳቸውን መከላከል በሚችሉበት ደረጃ ቢዋቀሩ ራሳቸውን ከጥቃት እንደሚታደጉ እየገለጹ ይገኛሉ። ህብረተሰቡ ይሄን ይበል እንጂ የታጣቂው ቡድን የሚይዛቸውን የጦር መሳሪየዎች በመመልከት፣ ‹‹ይሄን ቡድን የውጪ ሀይል ሳይደግፈው አይቀርም›› የሚል መላምት የሚያቀርቡ በርካታ ናቸው።

የታጣቂው ቡድን መሪዎች ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ተደረገ የተባለው ጥቃት እነሱ እንዳልፈጸሙ ገልጸዋል። ተጠያቂነቱንም ወደ መንግስት ሲያዞሩ ተደምጠዋል። ከዚህ ቀደምም በክልሉ ለተፈጸሙት ጥቃቶች ሀላፊነቱን እንደማይወስዱ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው የጸጥታ አካላትም ሆኑ የመንግስት ሀላፊዎች፣ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*