
አንድ ከተማ በውስጡ ከሚይዛቸው ጉዳዮች መካከል፣ የግልና የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ዋነኞቹ ናቸው። እነዚህ ተቋማት የበርካታ ዜጎችን የሥራ ዕድል እና የተርታው ማኅበረሰብ መገልገያ ጭምር መሆናቸው አይዘነጋም። በቀላሉ፦ ባንክ፣ ጤና ጣቢያ፣ ውሃ እና መብራት ለሕዝቡ ምን ዓይነት አገልግሎት እንደሚሰጡ የማያውቅ የለም። በርግጥ፣ ከሁሉም በላይ በንብረት ልክ የማይመዘነው ሰው በግፍ ተገድሏል።
ለዚያውም ከጥቃቱ በዕድል ለተረፈው የማኅበረሰብ ክፍል የሞራል ስብራቱ የማይረሳ አሳዛኝ ግድያ። አብዛኞቹ ድምፅ በሌለው መሳሪያ እና በከባድ መሳሪያ መገደላቸው ይታወሳል። ጥቂቶቹ ደግሞ በቤት ውስጥ እንደ ተራ ነገር ተቃጥለዋል። የዚህ ክፉ ዕጣፈንታ ከደረሳቸው የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አጣዬ ከተማ ተጠቃሽ ናት። ከተማዋ ከሌሎቹ የሚለያት ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ መውደሟ ነው።
ቢያንስ ከ400 በላይ የሚገመቱ የከተማዋ ቤቶች ተቃጥለዋል። ወደ 34 ሺሕ የሚጠጉ የከተማዋ ኑዋሪዎች ደግሞ መፈናቀላቸው ተጠቁሟል። ከዚህ ሁሉ እልቂት የተረፉ የከተማዋ ኑዋሪዎች ያለ ንብረት እና ያለመጠለያ ቤት እንዲሁም ያለ ምግብ ተቸግረው የመንግሥትን እና የወገን እርዳታን ለመጠበቅ ተገደዋል። በተለይም የምግብ እና ቁሳቁስ አፋጣኝ ድጋፍ ካልተደረጋቸው በሕይወት የመቆየታቸው ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።
Be the first to comment