
ኢትዮጵያ እንደ አገር ካልተሟሉላት ጉዳዮች መካከል የጤናው ዘርፍ ዋነኛው መሆኑን መሬት ላይ የሚታዩ ችግሮች ምስክር ናቸው።
አገራት በቀላሉ የሚቆጣጠሯቸው ወረርሽኞች ኢትዮጵያ ላይ ጉልበት አግኝተው ለዜጎች ከባድ ፈተና ሲሆኑ መታዘብ ተችሏል። በአቅራቢያቸው የጤና ተቋም ያላገኙ እናቶች በቤታቸው ከመውለዳቸው ጋር ተያይዞ እየሞቱ መሆኑን በተለያየ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ህፃናት የጤና ክትትል አጥተው በለጋ ዕድሜያቸው እየተቀጩ ነው። በተጨማሪም፣ ባሉት የህክምና ተቋማት ውስጥ የተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች ከታማሚው ብዛት አኳያ በቂ አለመሆናቸው ይነገራል። በዚህ ላይ አብዛኞቹ የጤና ባለሙያዎች በብቃት ተመዝነው የተመደቡ አለመሆናቸው ለታካሚዎች ሕይወት መጥፋት በመንስኤነት ይጠቀሳል። መንግሥት ይህን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ሲጠበቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል።
ሌላው ችግሩን አሳሳቢ ያደረገው ጉዳይ ለህክምና ሥራ ቅጥር ከብቃት ይልቅ ቋንቋ መመዘኛ ሆኖ መቅረቡ ነው። ሰሞኑን የዐማራ ክልል ሀኪሞች ያሰሙት ተቃውሞ ይህንኑ የሚያመላክት ነው። ዜጎች በተከበረ ሙያቸው ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ ያደረጋቸው ቀድሞ የተሰራው የዘር ፖለቲካ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። በመሆኑም፣ በክልሉ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ከተመረቁ የህክምና ‹ዶክተሮች› መካከል 400 የሚሆኑት ሥራ እንዳልተቀጠሩ ተነግሯል።
ሀኪሞቹ ባሰሙት አቤቱታ ላይ መረዳት እንደሚቻለው፣ ከዐማራ ክልል ውጪ ተቀጥሮ ለመስራት ሲንቀሳቀሱ፤ ክልሎች ከፌደራል የሥራ ቋንቋ በተጨማሪ፣ የራሳቸውን ቋንቋ መቻል የመጀመሪያ መመዘኛ ማድረጋቸው ሥራ ለማጣታቸው ምክንያት ሆኗል። በሚችሉት ቋንቋ ለማገልገል የዐማራ ክልላዊ መንግሥት ሲጠይቁም፣ «በጀት የለኝም» የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ያስረዳሉ። ‹‹በአነስተኛ በጀት ችግራችን መፍታት እየተቻለ ሰሚ አጥተናል›› የሚሉት የጤና ባለሙያዎች፤ በግል ተቀጥሮ ለመሥራት ሲሞክሩ ቢያንስ የሦስት ዓመት የሥራ ልምድ መጠየቃቸው ሌላኛው ፈተና ሆኖባቸዋል።
እንደ ሀኪሞቹ አስተያየት ያልተቀጠሩት ከብቃት ይልቅ ቋንቋ የሥራ ‹ክራይቴሪያ› ሆኖ መቅረቡ ሙያው እንዲጠላ ያደርጋል። ይህን ችግር በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለፅ ባለፈው ሰኞ ያደረጉት ሙከራ በፀጥታ ኃይሎች ክልከላ እንዳልተሳካ ተናግረዋል። ሰልፍ እንደሚያደርጉ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለአድማ ብተና፣ ለሰላም እና ደህንነት፣ ለብልፅግና ፓርቲ፣ ለርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት፣ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ለሲቪል ሰርቪስ እና ለሌሎችም በርካታ መስሪያ ቤቶች ካሳወቁ በኋላ መከልከላቸው አስቆጥቷቸዋል።
የዝግጅት ክፍላችን የክልሉን ጤና ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች አስተያየት ለማካተት በስልክ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካም።
ከዚህ በፊት ምደባ በፌደራል መንግሥት ይካሄድ እንደነበር የሚያስታውሱት ሀኪሞች፤ ምደባ በየክልል እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ የመጣ ችግር መሆኑን ለማስረዳት የሚከተለውን የተቃውሞ መፈክር አሰምተዋል፡- ‹‹የክልላችን ሕዝብ የተማረ ማምከን ይብቃ፣ ሀኪም የሌለው ክልል ሀኪም በቃኝ አለ፣ እኛ ዶክተሮች እንጂ ወንጀለኞች አይደለንም፣ ጆሮ ያለው መሪ እንሻለን፣ ለምን የዐማራ ዶክተሮች ብቻ አልተቀጠሩም? በዓለም አቀፍ ቋንቋ ተምረን ሳለ ለምን ብሔር ተጠየቅን? የጤና ባለሙያዎችን የሚያገል የጤና ፖሊሲ እንቃወማለን›› የሚሉት ይገኙበታል።
400 ያህል በህክምና ሙያ የተመረቁ ሀኪሞች ሥራ አጣን ብለው ሰልፍ ሲወጡ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አለመሆኑን በርካቶች ይስማማሉ። ከወላጆች አልፎ አገር ሀኪም ለማሰልጠን የምታወጣው ወጭ ከፍተኛ መሆኑ አይዘነጋም። በብዙ ዋጋ መክፈል የተማሩ ዜጎቿ መልሰው ካላገለገሏትም ኪሳራው እንዲህ በገንዘብ የሚተመን አይደለም። በመሆኑም፣ ከበርካታው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ዐማራ ክልል በተለያየ የጤና ቀውስ ውስጥ መኖሩ ተደጋግሞ ተዘግቧል። በተለይም በእናቶች የወሊድ ሞት ቀድሞ የሚጠቀሰው ክልሉ ነው።
በሌላ በኩል ሌሎች ወረርሽኞች እና ጎጅ ባሕሎችም የክልሉ ነባር ችግሮች ሆነው ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ መካከል ያለ ዕድሜ ጋብቻን ተከትሎ የሚከሰተው የማኅፀን ችግር አንደኛው ነው። ከዚህ ቀደም ያለ ዕድሜ ጋብቻ ለመፈፀም የዕድሜ ምርመራ ካደረጉት 585 ጥንዶች ውስጥ 169 ዕድሜያቸው ለጋብቻ ያልደረሱ በመሆናቸው ጋብቻቸው እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል። ሰሞኑን ደግሞ በምስራቅ ጎጃምና ሰሜን ወሎ ዞኖች በድብቅ ሊካሄድ የነበረ የ529 ያለ ዕድሜ ጋብቻ ተቋርጧል።
ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው ያለ ዕድሜያቸው እየተዳሩ ነው። ችግሩን የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፤ በሚፈለገው ልክ ለውጥ አልመጣም። በጉዳዩ ዙሪያም ትምህርት፣ ጤናና የፍትሕ ተቋማት ተቀናጅተው ባደረጉት እንቅስቀሴ ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው ሊዳሩ የነበሩ 480 ዕድሜቸው ያልደረሱ ልጆች ጋብቻ ከወላጆቻቸው ጋር በመወያየት ማቋረጥ ተችሏል።
ይሁን እንጂ፣ በየአካባቢዎቹ መረጃ ፈጥኖ ባለመድረሱ ምክንያት የ90 ህፃናት ጋብቻ መፈፀሙ ተጠቁሟል። ችግሩን በሕግ ለማስጠየቅ ቢሞከረም በማስረጃ ክፍተት የተነሳ የሚገባውን ያህል ተጠያቂ ማድረግ አልተቻለም ተብሏል። ያለ ዕድሜ ጋብቻ ሕገወጥ መሆኑን በአራያነት ያስተምራሉ ተብለው የሚገመቱ አንዳንድ ባለሥልጣናት፤ በሕፃናት ላይ የሚፈጽሙት ጋብቻ ከተርታው ዜጋ የተለየ አለመሆኑ፤ ችግሩን ይበልጥ እንዳወሳሰበው ተነግሯል።
በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሰውን የጤና ችግር ለመቅረፍ በጤና ባለሙያዎች የታገዘ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል። የጤና ተቋማትን ከመገንባት ተጨማሪ፣ የጤና ፖሊሲን እና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለዜጎች በሚመች መልኩ ማዘጋጀትም፤ ችግሩን ይቀንሰዋል ተብሎ ይታመናል።
Be the first to comment