
የአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኀበራዊ እንቅስቃሴዎች ዋንኛ ማዕከል የሆነችው አዲስአበባ፣ በውስብስብ ችግሮች ተተብትባ ተንገዳጋጅ ከተማ ከሆነች ሦስት ዐሥርታት አስቆጥራለች። ከነዋሪዎቿ መሰረታዊ ፍላጎቶች በተጻርዮሽ እንድትጓዝ መገደዷም፣ የከተማውን ሕዝብ ከአስተዳደርም ሆነ ከፖለቲካ ተሳትፎ ካገለለ የተጠቀሰውን ያህል ጊዜ ቆይቷል።
ለከተማ ሥነ-ልቦና ፍፁም ባይተዋር በሆኑ አባላቱ የተመሰረተው ኢሕአዴግ ሥልጣን ከጨበጠ ጀምሮ በአልቦ-ተወካይ የጫነባት የፖለቲካ ሥርዐት የችግሩቹ ሁሉ መነሾ ተደርጎ ይጠቀሳል። በተለይ በሕገ-መንግሥቱ ‹ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አለው› የሚል አንቀፅ መካተቱ፣ ዛሬ ላይ አገራዊ ፍርሰት ሊፈጥር የሚችል ከባድ ስጋት ደቅኗል። በዚህ ላይ፣ በቀጥተኛ ምርጫ ባልመረጠው አካል እንዲተዳደር የተበየነበት ፍርደ ገምድል ውሳኔ፣ ለመልካም አስተዳደር እጦት፣ ለፍትሕ መዛባት፣ ተጠያቂነት ለመጥፋቱ… ገፊ- ምክንያት ሆኗል።
አብዮታዊው ግንባር፣ በከተማይቱ ላይ የፈጸመውን ወንጀል የሚያገዝፈው በራሱ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 2 የአዲስ አበባ ነዋሪ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር መብት ከሰጠ በኋላ፤ ለይስሙላ እንኳ ተግባራዊ አለማድረጉ ነው። ሕገ-መንግሥቱ ፀድቆ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት (ከ1983 እስከ 1987 ዓ.ም ነሐሴ ወር ድረስ) ራሷን ችላ በክልልነት ተዋቅራ የነበረችው ከተማ፤ ይህ ጦሰኛ ሰነድ ከፀደቀ በኋላ የክልል አስተዳደሯን ተነጥቃ፣ ለኦሮሚያ ልዩ ጥቅም የምትቸር እና ተጠሪነቷ ለፌዴራል መንግሥቱ እንዲሆን መደረጉ፣ በከተማዋ ሕዝብ ላይ ለዘላቂው የተሸረበውን ሴራና የኢሕአዴግን ስር-ሰደድ ጥላቻ ያስረግጣል።
Be the first to comment