
በቅርቡ ታሪካችን ከመከኑ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር መልካም እድሎች አሁንም የተማርን አይመስልም። ፖለቲካችን ህመሙ እየጸና እንጂ፣ እየተፈወሰ አልዘለቀም። ይህ ለምን ሆነ? በታሪካችን የሽግግር ኹነቶችን ያጨናገፈው የትኛው ሾተላይ ነው? የዴሞክራሲ መሻቱስ ደጋግሞ የመከነው፣ የማይወልደውን እያረገዘ ነው ወይስ ያላረገዘውን እየወለደ?
የእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ሰፊና ዐውዳዊ ቢሆንም፤ የሽግግር ሂደቶቹ በአንድ ወገን ብቻ መመራታቸው እና በሽግግር ወቅት መመለስ የነበረባቸው መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ወደ ብሔራዊ ምርጫ መገፋታቸው በዋንኛነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
በሽግግር ወቅት የሚደረግ ምርጫ እና መደበኛ ምርጫ ምን እና ምን ናቸው?
በዋናነት የሽግግር ፖለቲካ ምርጫ፣ ከመደበኛው በተለየ ሂደት መደረግ እንዳለበት የፖለቲካ ንድፈ- ሀሳብና ተሞክሮ ያመለክታሉ። በዚህ ዐይነት ነባራዊ ዐውድ ውስጥ የሚደረግ ምርጫ ምን፣ መቼ ይደረግ፣ ከምርጫ በፊት ወይስ በኋላ፣ ቅድመ-ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?… የሚሉትን ጥያቄዎች፣ “በጋራ ውሳኔ ሰጪነት (pact transition)” መመራቱ ከሚጠበቀው ውጤት ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው። ውጤቱ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ሊሆን መቻሉ የሚመረኮዘው፣ በሚሰጠው ሕዝበ-ውሳኔ አሳታፊነትና በጋራ ስምምነት ላይ መመስረት አለመመስረቱ ነው። ምርጫው የታለመለትን መንትዮሽ ግብ ሊያሳካ የሚችልበትም ሆነ ጨንግፎ በተቃራኒው ለአገር መፍረስ ወይም ለአምባገነናዊ ሥርዐት መጽናት መንስኤ መሆኑ የሚወሰነውም በሂደቱ አሳታፊነት ነው። በሌሎች አገራት የሽግግር ተሞክሮ እንደተስተዋለው፣ በአመዛኙ በአንድ ወገን የፖለቲካ አሰላለፍ የተሸበበ የሽግግር ሂደት፣ የመጨረሻ መዳረሻው ሕዝባዊ ፍሬ ማፍራት ሳይሆን፤ አምባገነን መንግሥትን ማዋለድ ነው። በአንጻሩ አሳታፊ በሆነ ዐውድ በጋራ የተመራ የሽግግር ሂደት፣ ሕዝባዊ እና ዴሞክራሲያዊ ፍሬ የማፍራት እድሉ ሰፊ ነው።
Be the first to comment