በሙስጠፌ ወንድም ላይ የደረሰው ጥቃት እና ተያያዥ ጉዳዮች

የደጋሃቡር ጠቅላላ ሆስፒታል ‹ሜዲካል› ዳይሬክተር አብዱራህማን ሙሐመድ ዑመር ሰሞኑን ጥቃት እንደ ደረሰባቸው ተሰምቷል። ጥቃቱን የፈፀሙትም የቀድሞው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ ኢሌ ያዘጋጃቸዋል ተብለው ከሚጠረጠሩት ሰዎች መካከል አንደኛው ሳይሆኑ እንዳልቀረ ከስፍራው ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰው መረጃ ያመላክታል። ሰዎቹ ከዚህ ቀደም የግል ፀብ እንደሌላቸው ቢነገርም፣ ነገሩ የፖለቲካ ‹ኬዝ› እንዳለው ተጠቁሟል። ጥቃት የደረሰባቸው አብድራህማን በጅግጅጋ ሆስፒታል እየታከሙ ቢቆዩም፣ የተፈፀመባቸው የስለት ውጊያ ከባድ በመሆኑ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ተነግሯል። አብዱራህማን በሥራቸውም፣ በስብዕናቸው እና በሥነምግባራቸው የተመሰገኑ መሆናቸውን በቅርበት የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ። የጥቃቱ መንስኤን በተመለከተ እስካሁን ግልፅ መረጃ ባይወጣም፣ አብዱራህማን የአዲሱ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ ወንድም ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። በጥርጣሬ የተጠቀሱት የቀድሞው ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ ሰዎች በአቶ ሙስጠፌም ሆነ በአዲሱ የፖለቲካ ሥርዐት ደስተኛ እንዳልሆኑ ተነግሯል። ከዚህም አኳያ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጥቃቶችን ለማድረስ ወደኋላ እንደማይሉ ተጠቁሟል።

ሰሞኑን በአቶ አብዱራህማን ላይ ያደረሱት ጥቃት እንደ አንድ ማሳያ ተነስቷል። ጥቃቱን የፈፀመውም ሆነ ከእርሱ ጋር ተባባሪ ይሆናሉ ተብለው የተጠረጠሩ አካላት በሕግ ተይዘው እየተመረመሩ እንደሆነ ተዘግቧል። ከዚህ ቀደም በነበረው የፖለቲካ ሥርዓት ምክንያት፣ የአቶ ሙስጠፌ ወንድም ተገድለው እንደነበር የሚታወስ ነው። ወደ ሥልጣን በወጡ ሰሞን መግለጫ የሰጡት አቶ ሙስጠፌ በኃላፊነታቸው ዘመን የበቀለኝነት ሥራ እንደማይፈፅሙ ተናግረው ነበር። በዚህም በብዙዎች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ጨምሯል።

ፕሬዝዳንቱ ክልሉን በበላይነት መምራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በዐንፃራዊነት ለውጥ ማስመዝገባቸው ለተግባራዊነታቸው ሌላኛው ማሳያ ነው። የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈፀምበት የነበረው ሶማሌ ክልልን ሙሉ ለሙሉ ማዳን ባይቻሉም፣ ችግሩን ለመቀነስና ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ ከሚመለከተው አካል ጋር እየመከሩ ይገኛሉ። ሰሞኑን በሶማሌ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በሺር አህመድ ሃሺ የሚመራ ከፍተኛ የሶማሌ ክልል ማረሚያ ቤቶች አመራር አካላት፣ ለይፋዊ የሥራ ጎበኝት ሶማሊላንድ ማቅናታቸው የተጠቀሰው ዓላማ አንዱ አካል ነው ተብሏል።

የሶማሌ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን አመራር በሀርጌይሳ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሁኔታ ከመጎብኘታቸው በተጨማሪ፣ ከማረሚያ ቤቶች አመራር አካላት ጋር (በማረሚያ ቤቶች) አሰራር እና በታራሚዎች አያያዝ ብሎም በዜጎች ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።

ከላይ ለተጠቆሙት እቅዶች መሳካት የሕግ የበላይነትን ማስከበር እና አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ ቀዳሚ ሥራ መሆኑን በማመን በቅርቡ (አቶ ሙስጠፌ) ከጄል ኦጋዴን ፋውንዴሽን ኮሚቴዎች ጋር ምክክር አድርገው ነበር። በምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ጽህፈት ቤት እንደተደረገ የተነገረው ውይይት ላይ የፋውንዴሽኑ ተወካዮች እና የቀድሞ የጄል ኦጋዴን ተበዳዮች መሳተፋቸው ታውቋል። በውይይቱ ከለውጡ በፊት የነበረው የክልሉ አመራር በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ላይ ያደርስ የነበረው ኢ-ሰብአዊ በደል ተገምግሟል።

ተሳታፊዎቹ መንግስት ከለውጡ በኋላ አጥፊዎችን በሕግ ፊት ለማቅረብ የሰራውን ሥራ እውቅና ሰጥተዋል። የተሰጠው እውቅና በቂ ሥራ ተሰርቷል ለማለት ሳይሆን፣ ለማበረታቻ መሆኑ ተጠቁሞ፣ ወደፊትም አጥፊዎችን በሕግ ፊት በማቅረብ ብዙ ሥራ ከለውጥ አመራሩ እንደሚጠበቅ ተነግሯል። አቶ ሙስጠፌ በበኩላቸው፣ የክልሉ እና የፌደራል መንግስት የሕግ የበላይነትን የማስከበር እና አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ሥራን ያለመለሳለስ እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል። ይቅርታ እና ምህረት የመስጠት ሂደት የህዝብ ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሚተገበርም አያይዘው ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፣ ክልላዊ መንግስቱ አካባቢው ላይ ለዘመናት ከነበረው የፀጥታ ችግር ጋር በተገናኘ፣ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለማድረግ ተቸግሮ እንደኖረ ይታወቃል። በዚህ ረገድ ዐንፃራዊ ለውጥ ያመጡት አቶ ሙስጠፌ በመሰረተ ልማት ግንባታ በኩልም የተሻለ መነቃቃት ማሳየታቸው ለለውጡ ናሙና ነው ተብሏል። በዚያም ላይ አቶ ሙስጠፌ በክልሉ እየተሰራ ያለውን የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ሥራ አፈፃፀም በቅርቡ መጎብኘታቸው ይታወሳል።

በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች እየተሰሩ ያሉት የመስኖ፣ ተፋሰስ እና የግብርና መስረተ ልማት ፖሮጀክቶች፡- በ112 ሚልዮን ብር የተገዙ 50 የግብርና ትራክተሮች፣ በ111.3 ሚልዮን ብር የተገዙ 700 የሚሆኑ የተፋሰስ ውሃ ማሽኖች፣ እንዱሁም በ86.6 ሚልዮን ብር የተገዙ 17 የግብርና መሳሪያዎች (ማጓጓዥ ከባድ ተሽከርካሪዎች) ሲሆኑ፣ በድምሩ ከ309.9 ብር በላይ በክልሉ ተፋሰስ እና መስኖ ልማት ቢሮ የተገዙ የግብርና መስኖ እና ተፋሰስ ልማት ማሽነሪዎችን በመስክ ምልከታው ከተጎበኙት መካከል ይጠቀሳሉ።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*