ትኩረት የሚሹት ተፈናቃዮች

ሕወሓት፣ በሰኔ ወር አጋማሽ የፌዴራሉ መንግሥት ባወጀው “የተናጠል ተኩስ አቁም” ሽፋን መቀሌን በተቆጣጠረ ማግስት፣ ቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ፣ ኤርትራን ጨምሮ፤ በአፋር እና ዐማራ ክልሎች ላይ ጥቃት የመሰንዘር አቅድ እንዳላቸው በግላጭ ተናግረው እንደነበረ ይታወቃል። በዚህ መሠረትም፣ በአፋር እና ዐማራ ክልሎች ላይ በቀናት ውስጥ ድንገተኛ ወረራ ከፍተዋል። ይህም ሁለቱን ክልሎች ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል፤ አሁንም እያስከፈለ መቀጠሉን ልብ ይሏል።

የሕወሓት የሽብር ቡድን በወረራ በያዛቸውም ሆነ ገብቶ በወጣባቸው አካባቢዎች ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ኢ-ሰብዓዊ ግፎችን መፈጸሙን የሚያስረግጡ መረጃዎች በስፋት ወጥተዋል። የአጋምሳ፣ ጋሊኮማ፣ ጭና፣ ቆቦ፣ ደሴ እና የኮምቦልቻ ጭፍጨፋዎች፣ ለዚህ ጉልህ ማሳያ ይሆናሉ። በተለይም በዐማራ ክልል እየፈፀመው ያለው መጠነ ሰፊ ወረራ ከፍተኛ የሰብዓዊ እና የንብረት ጉዳት አድርሷል።

ሕወሓት በወረራቸው የአፋር እና ዐማራ ክልል አካባቢዎች የተፈፀሙትን ወንጀሎች በተመለከተ፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን ያደረጉትን ምርመራ ይፋ ማድረጉም የሚታወቅ ነው። ይህ ምርመራ የተደረገው ከመስከረም 5 ጀምሮ ሲሆን፤ በግኝቱ ላይ እንደተጠቀሰው፣ በሁለቱም ክልሎች ከጦርነቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው 483 ንፁሃን ሕይወታቸውን ሲያጡ፤ 165 የሚሆኑ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ሁለት መቶ ሃያ አራት (224) የሚሆኑት በዐማራ ክልል አካባቢዎች የተገደሉ ናቸው። የሚኒስቴሩ ምርመራ ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ፣ ተደራሽ ያልሆኑ ወረራ የተካሄደባቸው አካባቢዎች በመኖራቸው እና ጦርነቱ እየተባባሰ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ፤ የጉዳቱ መጠን ሊያሻቅብ የሚችልበት እድል ሰፊ እንደሆነም በግላጭ የሚታይ እውነታ ነው።

የሽብር ቡድኑ ለወረራ ሲነሳ ዋና ኢላማ ያረገው የዐማራ ክልልን እንደ መሆኑ መጠን፣ ከፍተኛ ውድመት የደረሰውም በዚህ ክልል ነው። በአሰቃቂ ግድያ ሕይወታቸውን ካጡ ሰዎች በተጨማሪ፤ የተደፈሩ እና አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ቁጥር ጥቂት እንዳልሆነ በተለያየ መንገድ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች አስረግጠዋል። አሰቃቂ የመብት ጥሰቶች እና ከሞራል ያፈነገጡ ድርጊቶችም መፈጸማቸው የተረጋገጠ ሃቅ ሆኗል። የመንግሥት እና ግለሰብ ንብረቶች ላይም የደረሰው ውድመት እጅግ ከፍተኛ እንደ ሆነ ሪፖርቱቹ በስፋት አሳይተዋል። የዐማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) ላይ ብቻ የደረሰውን ጉዳት ብንመለከት እንኳ፣ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ዘረፋ እና ውድመት እንደተፈጸመበት ተቋሙ ገልጿል።

Continue Reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*