የቅድመ ምርጫው ሂደት

መስቀለኛ መንገድ ላይ ሆና ‹ነፃ እና ዲሞክራሲያዊ› ምርጫ ለማድረግ ስትንደፋደፍ የከረመችው ኢትዮጵያ፣ ዜጎቿ በስጋት ውስጥ ሆነው ድምፅ ለመስጠት ሰዓታትን እየቆጠሩ ነው። ‹‹የኢትዮጵያ ችግር በምርጫ አይፈታም›› ከሚሉት አንስቶ ‹‹ምርጫው አሁን ካለንበት ማጥ መውጫ መንገዳችን ነው›› የሚሉትን ለሁለት ከፍሎ አከራክሯል። ‹‹አንዳንዶች ተገፍተው የወጡበት በመሆኑ ሁሉን አሳታፊ የሆነ ምርጫ አይሆንም። ብሔራዊ መግባት ይቅደም›› በሚል በርከት ያሉ ድምፆች ቢደመጡም፣ ጆሮ ተነፍጓቸው የምርጫው መደረግ አይቀሬ ሆኖ ወደ ሥራ ተገብቷል።

ስድስተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ በ2012 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ ቢታሰብም የኮሮና ወረርሺኝ ባሳደረገው ስጋት ወደ 2013 ዓ.ም እንዲራዘም ምክንያት ሆኗል። ምርጫው ለቀጣይ ዓመት መራዘሙን የተቀበሉት ቢኖሩም፤ ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ እስከ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድረስ ቅር ተሰኝተው እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ ቅር ከተሰኙ ፓርቲዎች መካከል፣ ለ27 ዓመታት የኢሕአዴግ አውራ ሆኖ ሲመራ የቆየው እና በቅርቡ በእንደራሴ ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተሰየመው ሕወሓት አንዱ ነው። የ2010ሩን ‹‹ለውጥ›› ተከትሎ ላለፉት ሥስት ዐመታት መቀሌ ገብቶ የመሸገው ቡድኑ፣ ምርጫው ለተጨማሪ አንድ ዓመት መራዘሙን ተከትሎ በክልሉ ምርጫ አድርጎ እንደለመደው ለመቶ ፐርሰንት በተጠጋ ውጤት ማሸነፉ አነጋጋሪ ነበር።

በወረርሺኙ ሰበብ የተነሳ ምርጫ አስፈፃሚው ተቋም ከፓርቲዎች ጋር ምክክር በማድረግ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ የተራዘመውን ምርጫ ለመከወን ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በጊዜ ሰሌዳው መሠረት፣ በግንቦት 28/2013 ዓ.ም የድምፅ መስጠቱ ሂደት የሚከናወንበት እለት እንዲሆን ተወስኖ እንቅስቃሴ ቢጀመርም ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ ልክ መንቀሳቀስ አልቻለም። በተለያዩ ችግሮች ባቀደው መርሃ ግብር ልክ መንቀሳቀስ ባይችልም እንኳ፣ ከዚህ በፊት ከነበሩት የምርጫ አስፈፃሚ ተቋሞች የተለየ እና ገለልተኛ ለመሆን ብዙ ስራዎችን መስራቱ አይካድም።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*