የተፎካካሪ ፓርቲዎች ‹‹መንቀሳቀስ አልቻልንም›› አቤቱታ

በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ከደጋፊዎቹ እና ከአባላቱ ጋር የሚያደርጋቸውን ስብሰባዎች በተደጋጋሚ እየተከለከለ መሆኑን ገልጿል። ይሄ የመንግስት አካሄድ ደግሞ በቀጣይ የሚደረገውን ሀገራዊ ምርጫም በጥርጣሬ እንዲያየው ሊያደርገው እንደሚችል በፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ገርባ በኩል አስታውቋል።

እንደ አቶ በቀለ አገላለጽ በአዳማ ከተማ ብቻ ለሦስተኛ ጊዜ ሰኞ የካቲት 23 2012 ዓ.ም ከአባላት እና ደጋፊዎቻቸው ጋር ሊያደርጉት የነበረው ውይይት ሳይሳካ ቀርቷል ብለዋል። በከተማዋ የሚገነባውን አዲስ ስታዲየምን ጨምሮ የመንግሥት የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ፓርቲው እንዳይጠቀምበት በመከልከሉ አባላት እና ደጋፊዎቻቸው ወደ መጡበት ለመመለስ መገደዳቸውንም ምክትል ሊቀ መንበሩ ጨምረው ገልጸዋል።

ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ጨምሮ የመንግሥት እና የሕዝብ ሃብትን በፍትሃዊነት ለመጠቀም የተደረሰውን ስምምነት የሚጣረሱ ተግባራት በመንግሥት ወገን እየተፈጸመ ነው ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል። የመንግሥት ኃይሎች የመንግሥት የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ከመከልከል ባሻገር የግለሰብ የመሰብሰቢያ አዳራሾችንም እንዳያከራዩ ጭምር አንዳስፈራሯቸውም አቶ በቀለ አስታውቀዋል።

በአዳማ ከተማ ከተደረገው ክልከላ ባሻገር አስቀድሞ በኦሮሚያ ክልል ሌሎች አካባቢዎችም ጠንከር ያለ ክልከላ ገጥሞናል ሲሉ አቶ በቀለ ተናግረዋል። እንቅስቃሴያቸውን ለመገደብ መንግሥት የሚያደርገው ተጽዕኖ በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ በቀጣዩ ምርጫ ተስፋ ማድረግ እንደሚቸግራቸው ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በአዳማ ከተማ ኦፌኮ የመሰብሰብ መብቴ አልተከበረልኝም ለሚለው አቤቱታ ምላሽ የሰጡት የከተማዋ ከንቲባ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ናስር ሁሴን ናቸው። እንደ አማካሪው ገለጻ «የኦፌኮንም ሆነ የየትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴ ለመገደብም ሆነ ለመከልከል መንግሥት መብቱ የለውም፤ የከተማ አስተዳደሩም ክልከላ አላደረገም» ብለዋል። ስለ ችግሩ መነሻም ሲያብራሩ ሁኔታው የተፈጠረው ኦፌኮ አዳራሽ ለመከራየት ከግለሰቦች ጋር የፈጠረው አለመግባባት እንጂ የመንግስት ክልከላ እንዳልሆነ በመግለጽ ቅሬታውን አስተባብለዋል።

የሰኞ የካቲት 23 2012 ዓ.ም ከፓርቲው ስብሰባ መስተጓጎል በፊት ሁለት ጊዜ ተፈጠረ የተባለውን ክልከላም አቶ ናስር እንደማይቀበሉት ይናገራሉ። የከተማዋን ስታዲየም ጨምሮ ኦፌኮ ከአባላትና ደጋፊዎቼ ጋር መገናኘት አልቻልኩም ማለቱንም የሚቃወሙት አማካሪው አዳራሾችን አስቀድመው በማሳወቅ መጠቀም ካለመቻል የሚፈጠሩ ክፍተቶች ለስሞታው መነሻ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በቀጣይም የትኛውም ፓርቲ አስቀድሞ በማሳወቅ ሁሉንም የመሰብሰቢያ ስፍራዎች ሊገለገልባቸው እንደሚችል አስረድተዋል።

በተደጋጋሚ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከአባላት እና ደጋፊዎቼ ጋር መነጋገር አልቻልኩም በማለት ቅሬታውን እያቀረበ የሚገኘው ኦፌኮ ጉዳዩ በዚሁ ከቀጠለ ቀጣዩ ምርጫም እንደሚያሳስበው ተናግሯል። ሆኖም፣ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም በሰጡት አስተያየት ኦፌኮ እያደረገ ያለው እንቅስቀሴ የምርጫ ቅስቀሳ መሆኑን በመጥቀስ ለክልከላው መነሻ መሆኑን ጠቅሰው ነበር። በአንጻሩ ኦፌኮ እያደረኩት ያለሁት ትውውቅ እንጂ ቅስቀሳ አይደለም በማለት በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና፣ አመራሮቼ ያለበቂ ምክንያት እየታሰሩብኝ ነው በማለት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ቅሬታ አቅርቧል። ከሀገር ውጪ በትጥቅ የታገዘ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየው እና ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ኦነግ የአባላቶቹ መታሰር እንዳሳሰበው እና ያለበቂ ምክንያት እንደታሰሩበት ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቋል።

ከፍተኛ አመራሮቹን ጨምሮ ዘጠኝ አባላቶቹ እንደታሰሩበት ኦነግ ቢያስታውቅም በአንጻሩ የኦሮሚያ ክልል ባስሥልጣናት ስለጉዳዩ እንደማያውቁ ተናግረዋል።

የኦነግ ቃል አቀባይ ቶሌራ አደባ እንዳሉት ‹‹መኖሪያ ቤታቸው (የአመራሮቹ) በሌሊት ነው የተከፈተው፤ ከፍተው ካሰሩ በኋላ ንጋት ላይ በመግባት እዚያ ውስጥ የሚኖሩትን በማስወጣት ረጅም ሰዓት የወሰደ ፍተሻ በማድረግ ዘጠኙን ሰዎች ወደ እስር ቤት ወስደዋል›› ብለዋል። እንደ አቶ ቶሌራ ገለፃ ለእስር ከተዳረጉት የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሎች መካከል አቶ ሚካኤል ቦረንና አቶ አብዲ ረገሳ እንዲሁም የማዕከላዊ ጽ/ቤት አባል አቶ ኬኔሳ አያና ይገኙበታል ብለዋል። በተጨማሪም፣ ሌሎች አባላት እና አማካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ እና የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ክፍል ሃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በበኩላቸው ስለ ጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል። የፌዴራል መንግስት ባለሰስልጣናትም እንዲሁ ስለጉዳዩ መረጃው የለንም ሲሉ ተናግረዋል።

ዘጠኝ ከፍተኛ አመራሮቼ ታስረውብኛል ብሎ ለመገናኛ ብዙሃን ያስታወቀው ኦነግ በነገታው ማክሰኞ የካቲት 24 2012 ዓ.ም ስምንቱ መፈታታቸውን የግንባሩ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ ተናግረዋል። እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ «የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አብዲ ረጋሳ በማስቀረት ሌሎች ስምንት ሀላፊዎች ተለቀዋል” ብለዋል።

የታሰሩበት ምክንያት ግን እስካሁን እንዳልተገለጸ የተናገሩት አቶ ቶሌራ በተመሳሳይ አመራሮቹ ከቀናት በፊት በቁጥጥር ስር ሲውሉም ሆነ ሲለቀቁ ምንም አይነት ምክንያት እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል። «ያለው የፖለቲካ ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ እና እየጠበበ መምጣቱን ነው የምንመለከተው” ብለዋል።

ኦነግ ትጥቅ ፈትቶ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኃላ በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀስኩኝ ነው ቢልም መንግስት በአንጻሩ በኦሮሚያ ክልል የሚፈጠሩ የሰዎች መሞት እና አለመረጋጋትን እያከናወነ የሚገኘው ኦነግ ነው በማለት ሲከስስ ይስተዋላል። እንደምክንያት የሚነሳው ደግሞ፣ የድርጅቱ አካል የሆነው (የነበረው) ኦነግ ሸኔ ለሚያደርሳቸው ጥቃቶች በግልጽ አለማውገዙን በማንሳት ይናገራል።

የተለያዩ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች እና ሰዎች መሞት የሚስተዋልበት የኦሮሚያ ክልል ለነዋሪዎቹ የተመቸ ባለመሆኑ በርካታ የክልሉ ተወላጆች አካባቢያቸውን ለቅቀው እየተሰደዱ ይገኛሉ። ምንም እንኳን የፌዴራል መንግስት እና የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ጉዳዩን ለመቆጣጠር እና ለማረጋጋት እየሰራን ነው ቢሉም አሁንም በተለይ በወለጋ አለመረጋጋት እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*