የውጪ እና የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ጉዳይ

እንቅፋቶች የበዙበት የዘንድሮው ምርጫ፣ የቅድመ-ምርጫ ሁነቶቹ ወደ መገባደዱ ተቃርበዋል። በቅድመ- ምርጫው ሂደት ከተስተዋሉ ዋና ዋና ክስተቶች መሃል የእጩዎች እስር እና ግድያ፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች በሥራ ገበታቸው አለመገኘት፣ የመራጮች ምዝገባ መጓተት፣ የአውሮፓ ህብረት ‹የታዛቢ ቡድን አልክም› ማለቱ… በዋንኛነት ይጠቀሳሉ።

የአውሮፓ ህብረት በተወካዩ በኩል ባለፈው ሳምንት እንደገለፀው ‹የታዛቢ ቡድን ለመላክ ለኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረብኳቸው ቅድመ-ሁኔታዎች ባለመሟላታቸው ታዛቢ ለመላክ አልችልም› ማለቱ ይታወሳል። የህብረቱ የውጭ ግንኙነት ቢሮ ቡድን መሪ በሆነው በጆሴፍ ቦሬል በኩል ባወጣው መግለጫ፣ ቁልፍ በሆኑ ሁኔታዎች ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መግባባት እንዳልቻለ ገልጿል። የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ፣ የአውሮፓ ህብረት እንደ ቅድመ-ሁኔታ ያስቀመጣቸው ሁለት ነገሮች የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚፃረር መሆናቸውን ይፋ አድርጓል። የመጀመሪያው፣ በህግ ያልተፈቀደ ከቴሌኮሙኒኬሽን ቁጥጥር ውጪ የሆነ ቪሳት የሳተላይት መሳሪያ ይዘው ለመግባት ከመጠየቁ ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ሁለተኛው፣ ከምርጫ ቦርድ አስቀድሞ ውጤቱን ለመግለጽ መፈለጉ እንደሆነ የሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ቃል-አቀባይ ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት ከሦስት ሳምንት በፊት የታዛቢ ቡድን እንደሚልክ ገልፆ የነበር ቢሆንም፤ ውሳኔውን ቀይሮ ታዛቢ መላክ አለመፈለጉን ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳውቋል። ይሁንና ይህን በተናገረ በሳምንቱ ደግሞ ውሳኔውን ቀልብሶ ታዛቢ (ስድስት አባላት ያሉት የኤክስፐርት ቡድን) እንደሚልክ መናገሩ የሳምንቱ አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኗል። ህብረቱ አቋሙን በምን ምክንያት ሊቀይር እንደቻለ ባይገለጽም፤ የኢትዮጵያ ምርጫ ላይ እጁን አስረዝሞ ፍላጎቱን ለመከወን አስቻይ ሁኔታ አለማግኘቱ፣ በአንድ አቋም እንዳይጸና ሳያደርገው እንዳልቀር ይገመታል። ሕወሓት-መራሾቹን አምስት የውሸት ምርጫዎች ለመታዘብም ሆነ ውጤቱ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ስለመሆኑ ለመናገር ያላፈረው ህብረቱ፣ ከእስከ ዛሬው በተሻለ ነፃ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት የተደረገበትን ኹነት ለመታዘብ አሻፈረኝ ማለቱ፣ አስተችቶታል።

Continue Reading

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*