የዳኞች ስሞታ እና ሥርዓት አልበኝነት

ዐማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በዳኞች ላይ ይፈፀማል የተባለ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ ተጠቁሟል፡፡ ጥቃቱ በፍትሕ መዋቅር ውስጥ ሕግን እንዲተረጉሙ በተመደቡ ዳኞች ላይ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ይህንን ድርጊት ይፈጽማሉ በተባሉ ግለሰቦች ላይም አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ክልላዊ መንግሥቱ አስታውቋል።

በቅርቡ የወረዳ ፍርድ ቤት የፍትሐ-ብሄር ዳኛ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ኪዳኔ እና ባልደረቦቻቸው ላይ የተፈፀመው ጥቃት እንደ ማሳያ ቀርቧል። አቶ ኤፍሬም ከሁለት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር (ከሥራ በኋላ) ቤተክርስቲያን ጸሎት አድርገው ባረፉበት ወቅት፣ ባልጠበቁት ሁኔታ ጥቃት እንደ ደረሰባቸው ለ‹ቢቢሲ› የአማርኛ ዜና ክፍል ገልፀዋል፡፡

በዱላ እና በተለያዩ ድምፅ አልባ መሳሪያ ጥቃት እንዳደረሱባቸው ጠቅሰዋል፡፡ ጉዳቱ ከጥርስ መርገፍ እስከ አፍንጫ መሰበር የደረሰ ነው ተብሏል፡፡ ዳኞቹ የጥቃት አድራሾችን ምክንያት እንደማያውቁ እና ባሉበት ድንገተኛ የሆነ ጥቃት እንደደረሰባቸው እንጂ፣ ከጥቃቱ በስተጀርባ ስላለው ሁኔታ ከመገመት ባለፈ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል።

ይሁንና ዳኞቹ የደረሰባቸው ጥቃት ከሥራ ጋር ተያያዥ እንደሚኖረው ይጠራጠራሉ፡፡ ከሥራ ውጭ ግላዊ ጸብ እንደሌላቸው ቢገልፁም በሥራ ሳቢያ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጠው የክልላዊ መንግሥቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ‹‹አስነዋሪ፣ አሳዛኝ እና አንገት የሚያስደፋ ድርጊት ነው” ሲል አውግዞታል፡፡

የችግሩ መንስኤን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡ መንግሥት “ዳኞች ውስብስብ መዝገቦችን በአግባቡ ለመወሰን ቀን ከሌት ከመሥራታቸውም ሌላ ሕገወጦች ጥቃት እያደረሱባቸው ነው። ጥቃቱም የመጀመሪያ ካለመሆኑም በላይ ዳኞችን ተስፋ ለማስቆረጥ ያለመ ነው›› ይላል። በተቃራኒው፣ አንዳንዶች በበኩላቸው ‹‹ዳኞች የፍርድ መዛባት አሊያም የፍትሕ ተባባሪ ካለመሆናቸው ጋር የተያያዘ ነው›› ሲሉ የመንግሥትን ገለጻ ያጣጥላሉ፡፡

በጥቃት አድራሾቹም ሆነ ጥቃት ተፈፀመብን በሚሉ ዳኞች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በሕግ የበላይነት ያለመዳኘት ችግር በሌላ ጎን ተነስቷል፡፡ በፍርድ አሰጣጡ (ፍትሕ) ተዛብቶብኛል የሚል ግለሰብ በዳኛ ላይ ጥቃት ማድረሱ እንደማይቀርም ተነግሯል፡ ፡ በመሆኑም፣ በየደረጃው ያሉ ዳኞች በሰው ሕይወት እና ንብረት ውሳኔ መስጠታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ መንግሥት ለዳኞችም ሆነ ለሕዝቡ ደኅንነት ሲል የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር ተጠይቋል። ጉዳት አድራሾቹም ተገቢውን ቅጣት ማግኘት እንዳለለባቸው ተያይዞ ቀርቧል።

የፍትሕ ሥርዓቱንም ሆነ የሕግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ እየወደቀ በመሆኑ፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና የጸጥታ አካላት ልዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል። በጉዳዩ ላይ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከቀናት በፊት መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። የክልሉ ዳኞች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ሥጋት ላይ ወድቆ በነበረበት ጊዜ ሳይቀር ያለማንም ተጽዕኖ በሕግ ብቻ ውሳኔ በመስጠት የዳኝነት አገልግሎቱ ላቅ እንዲል እየሠሩ መሆኑን በመግለጫው ላይ ተመላክቷል።

በማዕከላዊ ጎንደር፣ በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደር፣ በአዊ ብሔረሰብ፣ በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ በሚገኙ ዳኞች ላይ ጥቃት እና ተፅዕኖ ሲደርስ እንደነበር ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል። ጥቃቱ በተመቱት ዳኛ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በፍትሕ ሥርዓቱ እና በሕዝቡ ላይ እንደ ደረሰ ታስቦ መንግሥት እና ኅብረተሰብ ጥበቃ እንዲያደርግ ፍርድ ቤቱ ጠይቋል፡፡ ‹‹አለዚያ በዚህ መልኩ ከተሄደ [የፍትሕ] ሥርዓቱ ችግር ውስጥ ይወድቃል›› ሲል አሳስቧል፡፡

ከላይ የተጠቀሱ ችግሮችን የሚያጣራ ምርመራ ቡድን መቋቁሙ ተነግሯል። የምርመራ ቡድኑ በራሱ መንገድ በነጻነት ተንቀሳቅሶ በቅርቡ ወንጀለኞችን ለፍርድ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሕግ እና ሥርዓት የማፍረስ ተግባርን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ፣ ጥፋተኞች ለሕግ እንዲቀርቡ እና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ለሥርዓት አልበኝነት ሰበቦች

ሰሞኑን በአዊ ዞን፣ እንጅባራ ከተማ የቦንብ ፍንዳታ ተከስቶ የሁለት ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ግድያው የተፈጸመው ባል የቀድሞ ባለቤቱን ለመግደል በወረወረው ቦንብ መኾኑን የዞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል። በደረሰው የቦንብ ጥቃት ከሁለት ሰዎች ኅልፈት በተጨማሪ፣ በስፍራው የነበሩ 8 ሰዎች ቆስለው በእንጅባራ ሆስፒታል ሕክምናቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ታውቋል። የአካባቢው ሰዎች ጉዳዩ የግለሰቦች ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ ቤተ-እምነቶችን ለማቃጠል የታለመ እንደሆነ ይጠራጠራሉ፡፡

በተመሳሳይ፣ በሳንጃ ከተማ በሚገኝ የጉሙሩክ የፍተሻ ኬላ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተኮሱት ጥይት አራት ሰዎች መገደላቸውን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የኮምዩንኬሽን ፅህፈት ቤት አስታውቋል፡ ፡ ከዳንሻ ወደ ጎንደር የሚጓዝ የግል ተሽከርካሪ የታሸገ የዕቃ መጫኛ ለፍተሻ በጋራዥ ባለሙያ ለመክፈት ሲሞከር የጫነው ቦምብ ፈንድቶ አንድ ሰው መግደሉን ዞኑ አያይዞ ጠቅሷል።

የመኪናው አሽከርካሪ በዕቃ መጫኛው «ለምርምር እና ጥናት የሚሄድ አፈር» መጫኑን ቢገልፅም፣ በጉሙሩክ ባለሙያዎችና በጸጥታ አስከባሪዎች ተከፍቶ እንዲፈተሽ ተወስኖ ነበር። ሕይወቱ ያለፈው የጋራዥ ባለሙያ በተሽከርካሪው ላይ የተጫነውን ቦንብ በአጋጣሚ በመንካቱ ፈንድቶ ሌሎች ሦስት ጸጥታ አስከባሪዎች መቁሰላቸው ተገልጿል። በዚሁ ችግር ሳቢያ በዕለቱ የአካባቢው ነዋሪዎች በተኮሱት ጥይት ሁለት የጸጥታ አስከባሪዎች እና አንድ የጉሙሩክ ፈታሽ ተገድለዋል።

ከሕገ ወጥም ሆነ ከሥርዐት አልበኝነት ዜና ጋር በተያያዘ ያለ ሕጋዊ ፍቃድ በጎንደር ከተማ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጡ ነበር ተብለው የተጠረጠሩ 13 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተዘግቧል፡፡ በከተማው አንድ የካናዳ ግብረ-ሰናይ ድርጅት 13 ሰራተኞች ጊዜው ያለፈበትን መድሃኒት ሲያሰራጩ እንደነበር ተጠርጥረው መያዛቸው ተነግሯል፡፡ ተጠርጥረው ከታሰሩት መካከል ሁለት ኢትዮጵያዊ ሰራተኞች እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡ የካናዳው ግብረ-ሰናይ ድርጅት በበኩሉ ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት ባለሙያዎች የተማሩ እና ብቃት ያላቸው መሆኑን በመግለፅ በካናዳ ሲሰጡት ከነበረው የህክምና አገልግሎት የተለየ አልሰጠም ሲል በድህረ-ገፁ አስታውቋል፡፡

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*