
በአማራ ክልል የጸጥታ አካላት በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው ‹‹ህግን የማስከበር ዘመቻ›› ያደረገውን ከፍተኛ ተጋድሎና ህውሓት የሚያደርገውን የጦርነት ዝግጅት በመገምገም የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራቱን ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናግረዋል። ለበርካታ ዓመታት ክልሉ ሲጠቀምበት የነበረውን ሰንደቅ አላማ እንደሚያሻሽልም አስታውቀዋል።
አቶ አገኘሁ ይሄን የተናገሩት፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አምስተኛ ዙር ስድስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ጉባዔ መካሄድ በተጀመረበት የመጀመሪያ ቀን ነው። ታቅዶ በተሠራ የጥላቻ ትርክት የአማራ ሕዝብ በሚወዳት ሀገሩ እየተገደለ እና እየተፈናቀለ መሆኑን ተናግረዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ፣ በጉባዔው የክልሉን የግማሽ በጀት ዓመት ሪፖርትም አቅርበዋል።
የ‹‹ትህነግ የጥፋት እና የክህደት ቡድን›› የአማራ ሕዝብ እና መንግሥትን በጠላትነት ፈርጆ ሲንቀሳቀስ እንደቆየ አስታውሰው፣ ቡድኑ የአማራ ሕዝብ በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች እንዲጠላ እና በጥርጣሬ እንዲታይ አድርጓል። በተጨማም የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ወንድምና እህት የሀገሪቱ ሕዝብ ጋር በመቻቻል፣ በመዋደድ እና በመተባበር ላይ የተመሰረተ የሀገር ግንባታ ሂደት የራሱን አስተዋጽኦ እንዳያበረክት ሲሠራ ነበርም ብለዋል።
በዚህም ምክንያት የአማራ ሕዝብ በሚወዳት እና በሚሳሳላት ሀገሩ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልሎች ለ27 ዓመታት ታቅዶ በተሠራ የጥላቻ ትርክት ባፈራው ሀብትና ንብረት የባለቤትነት መብቱን ተገፎ እንዲፈናቀል ተደርጓል ሲሉ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።
Be the first to comment