
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በዕለተ-ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ይካሄዳል። በአቀራረቡ የተለየ ምርጫ ይሆናል ተብሎ በለውጡ ሰሞን የተለፈፈለት ምርጫና ሂደቱ፣ ባለፉት ሁለት ዐመታት በውዝግብ ታጅቦ እዚህ ደርሷል። በኢሕአዴግ መንፈራቀቅ ማግስት ተፈጥሮ የነበረው ብሔራዊ ተስፋ አሁን ላይ ወደ ብሔራዊ ሥጋት መቀየሩ፤ ምርጫው ወደ ከፋ አጣብቂኝ እንዳይከተን የሚያስጠነቅቁ በዝተዋል።
በ‹ኮቪድ-19› ሰበብ የተራዘመው ምርጫ ዳግም ቀውስ ውስጥ እንዳይከተን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። የምርጫው መራዘምን ተከትሎ በገዢው ፓርቲና በተቃውሞው ጎራ ውስጥ በሚገኙ የኦሮሞ ብሔርተኞች መካከል የተፈጠረው መቃቃር ለንፁሃን ሰዎች እልቂት መንስኤ ነበር። የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የነበረው ሕወሓት የምርጫ መራዘምን ከጅምሩ አክርሮ መቃወሙና ከብልፅግና ጋር ቅራኔ ውስጥ ከቶት እንደነበር ይታወሳል።
የሕወሓት ተናጠላዊ ውሳኔ ወስኖ ያካሄደው ምርጫ የልብ-ልብ ሰጥቶት፣ የሰሜን ዕዝን እንዲዳፈር ገፋፍቶት፣ ጦርነት እንዲቀሰቀስ አድርጎ አሁን በትግራይ ክልል ያለው ቀውስ መነሻ ሆኗል። የዚህ ምርጫ ጣጣ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ነባር መልኮች አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በታሪክ ያጋጠሙትን መልካም ዕድሎች እያከሸፈ መንጎድ መቀጠሉን ባለፉት ሦስት ዐመታት ጉዟችን አረጋግጠናል። በተስፋ የተጀመረው የለውጥ ምዕራፍ በዜጎች መፈናቀል፣ መጨፍጨፍና በእርስ-በርስ ጦርነት እየታጀበ የቁልቁለት ጉዞውን ተያይዞታል።
Be the first to comment