ምርጫ ወይስ አዛምድ?! – ዜናወርቅ ታፈረ

እንዳለመታደል ሳይሆን፣ እንዳለመረዳት፤ በአህጉራችን አፍሪካ፣ በተለይም በኢትዮጵያችን አገራዊ ምርጫ በደረሰ ቁጥር የምጽዓት ቀን ይመስል ዋይታና እሪታ ይበዛዋል። ይህ ዐይነቱ ሰቀቀነ ሲደጋገም በምርጫ ፖለቲካ ተስፋ መቁረጥ በማስከተሉ፣ አብዛኛው ሰው ‹መምረጥ፣ ካለመምረጥ ልዩነት የለውም› ወደማለት አዘንብሏል። በዚህም የገዥው አካል ቀንበር ፍቃደኛ ተሸካሚ መሆኑን መናገሩ ከቀባሪው ይልቅ፣ ለሟቹ ማርዳት ነው። መቼም በየትኛውም አገር የዴሞክራሲ መገለጫ ከሆኑት ውስጥ ቀዳሚው ነፃና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ነው። ምርጫ፣ መሾም ብቻ ሳይሆን፤ መሻርም እንዳለ ማሳያ ነው።

ከሰው መርጦ ለሹመት…

‹‹እንዳያማህ ጥራው፤ እንዳይበላ ግፋው፤›› እየሆነ በሄደው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ‹ነኝ› ማለት ሆኖ ከመገኘት ብዙ ማየል ርቋል። እናም፣ ሁሉም የፖለቲካ ፖርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የተበጠረ አስተሳሰባቸውን በጠራ አነጋገርና በግልጽ ቋንቋ ለመራጩ ሕዝብ በማስረዳት፣ ምርጫውን ከመንጋ ፍርድ የመታደግ ግዴታ ዋንኛ ሥራቸው ነው ተብሎ ይታመናል። ይህ ካልሆነ ግን፣ ለ‹ሹመት› የታሰበው ምርጫ፣ የሺሕ ሞት ንግሥና እንዳይሆን ያሰጋል። መራጩ ከቀረቡለት ከዕጩዎች መሀል የሚመርጠውን አጥቶ፣ በነሲብ ለውዳቂ ምራጭ እንዳይጋለጥ፣ ‹ምረጡኛ› ባይ ፓርቲ በሁለንተናዊ ጥንካሬና ብልጫ ተዘጋጅቶ መቅረብ እንዳለበት ማስታወሱም ጠቃሚ ነው። መቼም፣ የጉልቻ መለዋወጥ ወጡን እንጀራ ይዞ ለሚጠብቅ ተመጋቢ የተሻለ እንደማያደርግለት ከማናችንም የተሰወረ አይደለም። መራጩም የሚመርጠው አካል ‹ማር› ሲለው፣ ግራዋ እንዳይሆንበት ከወዲሁ የቤት ሥራውን ማጠናቀቅ ያስፈልጋል። አልያ፡-

‹‹እደግ፣ እደግ በለን ያሳደግነው ቀጋ

ዘመም፣ ዘመም አለ እኛውን ሊወጋ፤›› ሆኖ መበላት ሊመጣ ይችላል። ስለዚህም እውቀት ያለው ሥሌት፣ ብልሃት ያልተለየው አስተውሎት፣ ሥርዐት ያልጎደለው ዘዴ… የአሸናፊነትን መንገድ ለመጥረግ የግድ ነው። ፖለቲከኞች፣ አውቀን የምናምናቸው እንጂ፣ አምነን የምንቀበላቸው አይደሉምና፤ መልቲ ክፋትን ጥሎ፣ ‹‹melt Directions›› ማንጠልጠል ለአገርም ለሕዝብም ይበጃል።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*