ሰሜናዊት ጀግኒት  – ዶ/ር ኤልያስ ገብሩ አዕምሮ

ስኬት አይቀርም። ከጣሩ፣ ካመኑ፣ ተስፋ ካልቆረጡ በዓለም ላይ የማይሳካ ነገር የለም። በተቸረው ልዩ ኃይል ተቀስቅሶ የሰው ልጅ ወደፊት ከተጓዘ አንዳችም የሚሳነው ነገር እንደሌለ ታሪክ ይመሰክራል። ስኬታማ ሰዎች ለመውጣት ቀርቶ ለማሰብ ከሚያዳግቱ ረጃጅም የኑሮ ዳገቶች አልፈው ካለሙት ግብ ደርሰዋል። ከአካል ገፅታቸው ልቀው ለእምነትና ሩቅ ህልማቸው አድረው፣ በትዕግስት የልፋታቸውን ፍሬ አይተዋል። ረጃጅሞቹ ፈተናዎች ተፈጥሯዊ አልያም ሰው ሰራሽ ሊሆኑ ይችላሉ። ሰው ሰራሾቹ ዳገቶች መካከል ድህነት፣ ጦርነት፣ አምባገነናዊ አገዛዝና ኋላቀር አስተሳሰብን መጥቀስ እንችላለን። እንደ ማንዴላና ጋንዲ አይነት ታላላቅ ስኬታማ ሰዎች እነዚህን ፈተናዎች በድህነት ውስጥ እየተራቡ፣ እየታረዙ፣ አፈር ላይ እየተኙ አልፈው በጦርነት ወላፈን እየተገረፉ፣ በእስር ቤቶች ውስጥ እየታጎሩ ቢቀጡም እነሱ ግን የትዕግስት በትራቸውን ተመርኩዘው፣ በፍቅርና ይቅር ባይነት ተዋግተው አሸንፈዋል።

በሰው ሰራሽ ፈተናዎች ከሚፈተኑት በተቃራኒው ደግሞ ተፈጥሮ በራሷ ለየት አድርጋ የምትፈትናቸው ሰዎች አሉ። ያለምርጫቸው የተለያዩ የዘር በሽታዎችን ወርሰው፣ ከአማካዩ የሰው አካላዊ መጠን እጅግ ገዝፈው ወይም አንሰው፣ ከሰውነት አካላቸው የተወሰኑትን አጥተው ወደ ምድር የሚመጡ ሰዎች በርካታ ናቸው። ለእነዚህ ሰዎች እንደ ማንኛውም ሰው ኑሮን መግፋት በራሱ እጅግ በጣም ከባድ ፈተና ነው። አካል ጉዳተኝነትን እንደምሳሌ ብንወስድ የማየት ችሎታውን የተነፈገ አንድ ሰው ልበ ብሩኸ እስካልሆነ ድረስ ተፈጥሮ የጋረጠችበትን የህይወት ጨለማ ለማሸነፍ ያታክተዋል። የመስማት ችሎታውን በተፈጥሮ የተነፈገ ሰው ደግሞ፣ የዓለምን ጥልቅ ምት ማዳመጥ የሚችል ክፍት ህሊና ከሌለው ኑሮ ምን ያህል ፀጥ ያለች እንደምትሆንበት መገመት አይከብድም። መስማት ለማይችለውም ሆነ ማየት ለተሳነው አካል ጉዳተኛ ህይወት ብርታትን የምትጠይቅ የቀን ተቀን ፈተና ነች።

እስኪ አሁን ደግሞ እራሳችሁን ማየትም፣ መስማትም በማትችል ወጣት ሴት ውስጥ አድርጋችሁ ሳሉት። እንኳንስ የእሷን ቦታ ይዞ መኖር ይቅርና ማሰብ በራሱ ሞት መስሎ ታይቷችሁ ይሆናል። ሁለቱን ዋና ዋና የስሜት ህዋሳት ዓይንና ጆሮን አጥቶ መኖር ከበድንነት የማይለይ መስሎ ሊታያችሁም ይችላል። በጭለማና ፀጥታ የተዋጠ መቃብር ውስጥ የተቀበረ በድንነት። እንደዚህ ሆኖ ከተሰማችሁ ለእናንተ የህይወት መገለጫ የስሜት ህዋሳት ብቻ ናቸው ማለት ነው። የዛሬዋ ተዘካሪያችን ወጣት ሀበን ግርማ፣ ይህንን መሰል ግምቶችን ሙሉ በሙሉ የሻረች ጀግኒት ነች። ህይወት ማለት ከስሜት ህዋሳት ያለፈች ረቂቅ ሚስጥር እንደሆነች በተግባር አስመስክራለች። በዓይኗ ብርሃን ባትመለከት በብሩኽ ልቧ እያስተዋለች፣ ወደ ጆሮ ታምቡሯ ድምፆች ባይደርሱም በክፍት ህሊናዋ የዓለምን ሪትም እያዳመጠች ስኬታማ የሆነች በደም ኢትዮ- ኤርትራዊት በዜግነት አሜሪካዊት ሴት ናት። ከስሜት ህዋሳት ያለፈች ሰሜናዊት ጀግኒት!

1975 ዓ.ም እ.አ.አ የበጋ ወራት ውስጥ የሰሜኗ ኮከብ ወ/ሮ ሳባ ገብረየሱስ የኤርትራ ኑሮ በቃኝ ብላ ከቀዬዋ ተሰደደች። የደርግን አገዛዝ በመገርሰስና ነፃነትን በማወጅ ፍላጎት ተፀንሶ ሊያባራ ያልቻለው ጦርነት ሰላም ቢነሳትም የሳባ ዋነኛ ብሶት ግን ይህ አልነበረም። ይበልጥ ያሳሰባት የታቀፈችው ጨቅላ የወደፊት ህይወት ነበር። ገና ነፍስ ያላወቀው ልጇ ሙሴ ገብሬ እይታው እንደተጋረደና መስማት እንደማይችል ያወቁ የመንደሯ ሰዎች እንደተረገመች ማንሾካሾክ ከጀመሩ ወራት አልፈዋል። የሐሜቶቻቸው ማካበቢያ፣ የቡና ላይ ወሬ አፍ ማሟሻቸው አድርገዋታል። ከሽሙጣቸውና ግልምጫቸው ለመሸሽ ብቸኛ አማራጯ ስደት ሆነ። የእርግማን ውጤት ነው የተባለውን ልጇን ይዛ ከኤርትራ ወጣች። ወደ ሱዳን አቅጣጫም ጉዞ ጀመረች። በየቦታው ከሚያጋጥሟት የባሩድ አረሮች እያመለጠች በቀን ትጓዛለች። ሌሊቱን በጅቦች ጩኽት ታጅባ ከዛፍ ጥላ ስር ጋደም ትላለች። የሞትን አፍንጫ እያሸተተች መንገዷን ቀጠለች።

2006 ዓ.ም እ.አ.አ ታህሳስ ወር፣ ‹ዋይት ሀውስ› ብለው ቀደምት የገዢ መደብ አሜሪካውያን በሰየሙት ቤተ-መንግስት ውስጥ ሁለት ብርቅዬ ጥቋቁር ሰዎች እየተወያዩ ነበር። አንደኛው ሰው የመጀመሪያው ጥቁር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሲሆን ሁለተኛዋ ሰው ደግሞ የለውጥ ቻምፒዮን ተብላ የተሸለመችው ሀቤን ግርማ ነበረች። ሀበን ወደ ቤተ-መንግስቱ በክብር እንግድነት የተጠራችው የሀያ አምስተኛውን ዓመት የአሜሪካን የአካል ጉዳተኞች ንቅናቄን (Americans with Disabilities Act)ምስረታ አስመልክቶ ነበር። ማየቱና መስማቱ ባይሆንላትም እድሜ ለዘመን ወለድ ቴክኖሎጂዎች ከኦባማ ጋር በደንብ እየተግባባች ነው። እሱ በዲጂታል ማሽኑ የሚፅፍላትን መልዕክት ማሽኑ ወደ ብሬል ፅሁፍ ቀይሮ ያቀርብላታል። ጥቁሩን ፕሬዝዳንት እንዲህ አለችው – “አየኽ አይደል ቴክኖሎጂ ምን ያህል የአካል ጉዳተኞችን ክፍተት ሞልቶ የሚያሻግር ድልድይ እንደሆነ?” ባራክ ሁሴን ኦባማ በግርምትና በአድናቆት እያያት በሀሳቧ እንደሚስማማ ገለፀላት። ዳሩ፣ በሀበን ፅናትና ችሎታ የማይገረምና የማይደነቀ ማንም የለም።

ተወዳሻችን ሀበን ግርማ የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያዋ ማየትም መስማትም የማትችል የህግ ምሩቅ ተማሪ ነች። በትምህርቱ ረገድ ይህንን ውጤት ከማስመዝገቧም በላይ ለሷ አይነት አካል ጉዳተኞች ቀርቶ ለሌላውም ሰው አዳጋች የሚባሉ ነገሮችን አድርጋለች። ተራራዎችን እየተንጠላጠሉ መውጣትና ጀልባዎችን መቅዘፍ የመሰሉ አደገኛ ድርጊቶችን ሳይቀር ተግብራለች።

ከዋይት ሀውስ ጉብኝቷ ጥቂት ቀናት በኋላ ታላቁ የጎግል ካምፓኒ ባቀረበላት ጥሪ መሰረት ሄዳ ንግግር አቅርባ ነበር። በፕሮግራሙ ላይ ሀበን እዚህ ደረጃ ላይ እንዴት እንደ ደረሰች ስትጠየቅ ሶስት ባለውለታዎች እንዳሏት ገለፀች። የአሜሪካ የአካል ጉዳተኞች ንቅናቄን፣ ቻኮሌት ኬክንና ባለ ውለታዋ እናቷን።

ወ/ሮ ሳባ ገብረየሱስ የሞት ሽረት ትግላቸውን አልፈው በአንድ ካቶሊካዊ የእርዳታ ድርጅት ድጋፍ አሜሪካ ይገባሉ። ከልጃቸው ከሙሴ ጋር ትንሽ ጊዜ ከኖሩ በኋላ ከአቶ ግርማ ጋር ይተዋወቃሉ። ኮከባቸው ገጠመ። ኢትዮጵያና ኤርትራ በመነጣጠል ጫፍ ላይ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያዊው ግርማና ኤርትራዊቷ ሳባ በፍቅር አንድ ሆኑ። ፅንስ ተቋጠረ። የመዋደዳቸው ፍሬ ጎምርቶ ሲፈካ ቆንጅዬ ሴት ልጅ ሆነች፤ ስሟንም ሀበን አሏት። 1980 ዓ.ም መሆኑ ነው። ይህቺ ትንሽ መልዓክም ለቤቱ አዲስ ደስታ ሆነች። ከጊዜ በኋላ ግን ሀበን የታላቅ ወንድሟ ሙሴ እጣ ፈንታ እንደደረሳት አወቁ። ‹እርግማን ይሆን እንዴ?› ብለው በአንድ በኩል እድላቸውን ቢጠራጠሩም በሌላ በኩል የአካል ጉዳተኛ መብት በደንብ የሚጠበቅባት የአማራጮች ምድር አሜሪካ ውስጥ መሆናቸው ተስፋቸው እንዳይጠፋ አፅናናቸው። ሀበን በቁመትና በጭንቅላት እያደገች ስትመጣ የቤተሰቡ በረከት እንጂ እርግማን አለመሆኗን ማስመስከር ጀመረች። ህገ መንግስቱ ለእሷና መሰሎቿ ያጎናፀፈውን መብት ተጠቅማ በኦክላንድ ትምህርቷን ጀመረች። በየቀኑ ለአንድ ሰዓት የብሬል ስልጠናዋን እየወሰደች በቀለሙ ት/ት ዘለቀች።

ታዲያ 15 ዓመት ሲሞላት የእናት ምድሯ የአፍሪካ አየር ጠራት። ቤተሰቦቿ ባይስማሙበትም ከአንድ የበጎ አድራጎት ቡድን ጋር ወደ ማሊ ለመሄድ ወሰነች። ማሊ ሄዳ ለ800 ህፃናት የሚያገለገል ት/ቤት በመስራቱ ሂደት ላይ ተሳተፈች። ለመማሪያ ክፍሎቹ መስሪያ የሚሆነውን አፈርና አሸዋ በጣቶቿ ስትዝቅ የተሰማት ደስታ እጅግ ግሩም እንደነበር በተለያዩ አጋጣሚዎች ላይ ተናግራለች። ሀበን ወደ ሀገሯ አሜሪካ ተመልሳ ት/ቷን በመቀጠል ለተሻለ ት/ት ወደ ፖርትላንድ ሌዊስ ክላርክ ኮሌጅ ገባች። በዚህ ኮሌጅ በነበራት ቆይታ አንድ ገጠመኝ ነበራት። የመመገቢያ ሰዓት ሲደርስ ወደ ምግብ አዳራሹ መሄድ የቀን ተቀን ተግባሯ ነበር። ታዲያ መመገቢያ ካፌው በሚያዘጋጀው ሜኑ ላይ ያሉት የምግብ ዝርዝሮች በብሬል መልክ አልተዘጋጁም ነበር። ስለዚህ፣ ርሀቧን ለማስታገስ ወደ ካፌው ባቀናች ቁጥር የቀረበላትን ነገር ያለ ምርጫ መብላት ግዴታዋ ነበር። የምትወደውን ቸኮሌት ኬክ ማግኘት አልሆነላትም። ብዙ ጊዜ ለካፌው አስተዳደሮች ሜኑዉን በብሬል እንዲዘጋጅላት ብታመለክትም ተጨባጭ ውጤት ታጣለች። ገንዘብ ከፍላ የምትመገበውን ምግብ መምረጥ አለመቻሏ ስላንገበገባት በህግ መብቷን ጠየቀች። እንደማንኛውም ሰውም መብቷን አስከበረች።

ይህቺ ጥቁር እንቁ በአሁኑ ወቅት በቤርኒሌይ ካሊፎርኒያ የአካል ጉዳተኞች መብት ዋና ነገረ ፈጅ ሆና ትሰራለች። በ2016 የፎርብስ ምርጥ ተጽእኖ ፈጣሪ ወጣቶች መካከል ተካታለች። እሷና ታላቅ ወንድሟ ሙሴ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ የማነቃቂያ ንግግሮችን ያደርጋሉ። በ2007 ታህሳስ ወር ላይም ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዲሃኪ ካምፓስ ለሚገኙ ተማሪዎች ተሞክሮዋን አካፍላለች። እድሜ ይስጣት እንጂ ገና ለብዙዎች የጽናት ተምሳሌት ሆና ትጠቀሳለች። የሁሉም ይቻላል እውነተኛ ተምሳሌት፤ በደም ኢትዮ-ኤርትራዊት፣ በዜግነት አሜሪካዊት። ከስሜት ህዋሳት ያለፈች ሰሜናዊት ጀግኒት!

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*