
የባልደራስ አጠቃላይ የምርጫ ዝግጅት ምን ይመስላል?
ባልደራስ ወደ ምርጫ ለመግባት ጥሩ ቁመና ላይ ነው ያለው። ጥሩ የሚባል የተብራራ ማንፌስቶ አዘጋጅተናል። ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የተማሩ እና መልካም ሥነ-ምግባር ያላቸውን በቂ እጩዎችንም አዘጋጅተናል።
በአዲስ አበባ ምን ያህል እጩዎችን ለከተማው መስተዳድር እና ለፓርላማው ታቀርባለችሁ?
በከተማው መስተዳድርም ሆነ በፓርላማው መቀመጫ ቁጥር ልክ እጩዎችን አዘጋጅተናል።
የባልደራስ ዋነኛ አጀንዳዎች ምን ላይ ያጠነጥናሉ?
አንደኛው የአዲስ አበባ የመዋቅር ችግርን መፍታት ነው። ይኸውም በኢኮኖሚው ትልቅ አበርክቶ ያላት አዲስ አበባ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ቀመር በሚቀመርበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምንም ቦታ እንዳይኖራት ተደርጓል። እንዲሁም አዲስ አበባ ክልል መሆን ሲገባት፣ ሆን ተብሎ እንደ አነስተኛ ከተማ እንድትታይ ነው የተበየነባት። እናም በምርጫው አሸንፈን እነዚህ ሁሉ እንዲስተካከሉ እናደርጋለን። በጠቅሉም ባልደራስ አዲስ አበባን ማዳን፣ ኢትዮጵያን ማዳን ነው ብሎ ያምናል።
ሌላው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የምንሰጠው ትኩረት ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው የመልካም አስተዳደር እጦት አዲስ አበባን ጨምሮ፣ በመላ አገሪቱ ዘመኑን የሚመጥን የልማት አውታር እንዳይዘረጋ ዋንኛ እንቅፋት ሆኗል። ይህንን ለመቀየር ከሕዝባችን ጋር አበክረን እንሠራለን።
ባልደራስ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በአዲስ አበባ ላይ የሚያነሳውን ልዩ ጥቅምንም ሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ፍፁማዊ የባለቤትነት ጥያቄ የተቀየረውን አጀንዳ እንዴት ያየዋል?
በአዲስ አበባ “ልዩ ጥቅም” ብሎ የሚነሳ የአንድ ቡድን የባለቤትነት ጥያቄ፣ አገር አፍራሽ ከመሆኑም በዘለለ፤ በከተማይቷ ለሚኖረው ሰፊው ማኀበረሰብ ክብር የማይሰጥ፣ በጣም ስስታም እና ስግብግብ የሆነ አስተሳሰብ ነው።
አዲስ አበባ የእኛ የኢትዮጵያውያን የጋራ ቤታችን ናት። ሁላችንም በጋራ እና በዕኩልነት ልንኖርባት ይገባል። ስለዚህም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በአዲስ አበባ ላይ በተናጠል የሚያነሳውን “ልዩ ጥቅም”ንም ሆነ ወደ ፍፁማዊ “ባለቤትነት” ያሸጋገረውን ፖለቲካ፣ ምርጫውን በማሸነፍ ሙሉ በሙሉ እናመክነዋለን።
Be the first to comment