‹‹ኢትዮጵያ ለ110 ሚሊዮን ሕዝብ እናት ነች›› ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ አያሌው (የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት)

እናት ፓርቲ መቼ ነው የተመሰረተው? “እናት” ብላችሁ የሰየማችሁበት ምክንያትስ ምንድነው?

የእናት ፓርቲ ምስረታው ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ ነው። ጽንሰ-ሃሳቡ በብዙዎች ኢትዮጵያውያን ውስጥ የነበረ ነው። ጥንስሱ በ2011 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ ፈቃድ አግኝተን እንቅስቃሴ የጀመርነው በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ነው። የመስራች ጠቅላላ ጉባኤ ደግሞ የካቲት 29/2012 ዓ.ም አድርገናል። ይህም ሆኖ ከቦርዱ የምስክር ወረቀት ያገኘነው ከረጅም ጊዜ በኋላ ጥር 10/2013 ዓ.ም ነው።

ለፓርቲያችን “እናት” የሚል ስያሜ የሰጠነው ‘ኢትዮጵያ ለሁላችንም፣ ለ110 ሚሊዮን ሕዝብ እናት ነች’ ብለን ስለምናምን ነው። እናም፣ ይችን እናት መታደግ ያስፈልጋል። አስተምራናለች፣ ተንከባክባናለች፤ አሁን ደግሞ ወደ ላቀ ደረጃ ልናደርሳት ይገባል።

እናት፣ ጎበዝ ልጆች እንዳላት ሁሉ፣ ሰነፍ ልጆች አሏት። ታታሪ ልጆች እንዳላት ሁሉ፣ ዳተኛ ልጆች አሏት። ጥቁር፣ ቀይ፣ የቀይ ዳማ መልክ ያላቸው ልጆች እንዳሏት ሁሉ፤ በልጆቿ መካከል አድሏዊነት የላትም። ጥሩውም የእርሷ ልጅ ነው። ጥሩ ያልሆነውም የእርሷ ልጅ ነው። ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ ሁሉንም ወደ አንድ የሚያመጣ እንደዚህ ዐይነት የእናትነት ባህሪ የተላበሰ የፖለቲካ ፓርቲ በጣም አስፈላጊ ነው።

የእናት ፓርቲ ዋና ዋና አጀንዳዎች ምን ላይ ያተኩራሉ?

ከዓለም ቀደምት ስልጣኔዎች ኢትዮጵያ አንዷ ነች። እንደ መንግሥት፣ ረጅም የመንግሥትነት ታሪክ ያላት አገር ነች። ይህ ሆኖ ሳለ፣ ዛሬ የምንታወቀው በረሃብ፣ በርዛት፣ በመፈናቀልና በመሳሰሉት በጎ ባልሆኑ ገፅታዎቿ ነው። ለዚህ ደግሞ ተፈጥሮ ካመጣብን መከራ በላይ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በራሳችን ላይ ያመጣነው ችግር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። አገራችን ካለፉት 50 ዐመት ጀምሮ በ“እኛ” እና በ“እነሱ” ተከፋፍላ እየኖረች ነው። እኛ አብዮተኞች፣ እነሱ ፀረ-አብዮተኞች፤ እኛ ተጨቋኝ፣ እነሱ ጨቋኝ፤ እኛ አድሀሪ፣ እነሱ ተራማጅ… ተባብለን የመጀመሪያዎቹን 17 ዐመታት በባዕድ ርዕዮተ-ዓለም ስንጠፋፋ ኖረናል። ይህ ትርክት ዛሬም አላበቃም።

በድኀረ-ድርግ ደግሞ የ“እኛ እና የ“እነሱ” የሚለው ክፍፍል ሌላ ገፅታ እንዲላበስ ተደርጓል። እኛ የእዚኛው ቋንቋ ተናገሪዎች፣ እነሱ የእዛኛው ቋንቋ ተናጋሪዎች፤ አንዱ ጨቋኝ፣ ሌላኛው ተጨቋኝ በማለት ሕዝባችንን ከፋፍለነዋል። በዚህም በደርግ ከነበረው በላይ፤ በብዙ እጥፍ የሚሆኑ ወገኖቻችንን በዚህ 30 ዐመት ውስጥ አጥተናል።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*