“እንወርዳለን” – ዳዊት ኃይሌ

ሰሞኑን የግል ጉዳይ ለማስጨረስ በአንድ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ፅሕፈት ቤት ስመላለስ ነበር። የግቢው ቢሮክራሲ ያሰለቸው ህዝብ፣ ሲገባና ሲወጣ፣ ጉዳዩ እስኪያልቅለት በተሰላቸ ፊት ቆሞ ሲጠባበቅ ይታያል። በዚህ መሀል ነበር አጠገቤ የተቀመጠው ደላላ “ችግር የለውም፣ እንወርዳለን፣ ቶሎ ይለቅለት” ሲል የሰማሁት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‘እንወርዳለን’ የሚል የአራዳ ቋንቋ ጉዳይ ለመጨረስ (በተለምዶ ‘ለመግደል’) አይነተኛ መፍትሔ እየሆነ መጥቷል። አንዳንዴም ‘እንለቃለን’፣ ‘እንበጥሳለን’ የሚሉት ቃላት በተለዋጭነት ጥቅም ላይ ሲውሉ መስማት የተለመደ ነው። ቁጥራቸው ቀላል በማይባል መስሪያቤቶች ውስጥ አንድ ባለጉዳይ ጉዳዩን ለመጨረስ ‘በእግሩ ሳይሆን በእጁ መሄድ’ ግዴታ እየሆነበት መጥቷል። አንድ ጓደኛዬ ከገንዘብ ውጭ ጉዳይህ እንዲያልቅልህ ክፍለከተማ ውስጥ ሁነኛ ሰው ሊኖርህ ይገባል ለማለት፡- “ከእያንዳንዳችን ቤተሰብ አንዳንድ ሰው ክፍለ ከተማ ውስጥ ካልተቀጠረ ጉዳያችን አያልቅልንም” ሲል በቀልድ መልክ አጫውቶኛል።

ታዲያ በዚህ ጉዳይ የመንግስት ሰራተኞችን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ መስሎ አይታየኝም። ፈረንጆች እንደሚሉት “It takes two to tango” (‘ታንጎ’ የተሰኘው ዳንስ በሁለት ሰዎች ይደነሳል)። ሰጪ ከሌለ ተቀባይ አይኖርም። “መሬት አስተዳደር ውስጥ የሚገኘው ፋይልህ ጠፍቷል” የተባለ የቤት ባለቤት ፋይሉን ለማስፈለግ ገንዘብ ለመስጠት አይኑን የማያሽ ከሆነ፣ ቀጥሎ ፋይሉን ደብቀው ጠፋ እንደማይሉት ምንም ዋስትና የለውም። አንድ ህግ-አክባሪ ሰራተኛ “ህጉን ተከትዬ ነው የምሰራው” ብሎ በዘመኑ ቋንቋ ‘ግግም’ ካለ፣ ዳጎስ ያለ ጉርሻ ፈልጓል ማለት ነው በሚል እሳቤ መጠኑ ከፍ ያለ መማለጃ በአማላጅ በኩል ይላክለታል። በአቋሙ ፀንቶ አልተባበርም ካለ ደግሞ ጨለማ ከብርሀን ጋር ህብረት የለውም እንዲሉ ጨለማው ስራቸውን ሳያጋልጥባቸው ምክንያት ፈጥረው ከስራው እንዲቀነስ ያደርጉታል። መንግስት በየጊዜው የሚያወጣቸው ምክንያታቸው ግልፅ ያልሆነ አሳሪ ህጎች ለአንዳንድ መንግስት ሰራተኞች በዘመኑ ቋንቋ ‘ቢዝነስ ለመስራት’ እድሉን አመቻችቶላቸዋል። በቅርቡ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ኮንዶሚንየም መገበያየት እንጂ ስም ማዞር ለተወሰነ ጊዜ ከልክሏል። ታዲያ ይኼ አጋጣሚ ለአንዳንድ የመስተዳድሩ ሰራተኞች አዲስ ገበያ ፈጥሮላቸዋል። የሽያጭ ውሉ አዋጁ ከወጣበት ቀን በፊት እንደተከናወነ በማስመሰል ስም ለማዞር ባለጉዳዮች ከአስራ አምስት እስከ ሀያ ሺህ ብር እንደሚጠየቁ ሰምቻለሁ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢሚግሬሽን መስሪያቤት ወደ ውጭ መውጣት የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት ለሌላቸው ዜጎች ፓስፖርት እንዳይሰጥ ከልክሎ ነበር። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አንዳንድ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ዳጎስ ያለ መማለጃ በመቀበል ፓስፖርት እያተሙ ይሰጡ እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው።

በቅርቡ ግንባታቸው ተጠናቆ ስራ የጀመሩት የክፍለ ከተማ ህንፃዎች ላይ ለጌጥ ተብሎ የተለጠፈው እምነ በረድ እየወደቀ ወደ ህንጻው በሚገቡትና በሚወጡት ተገልጋዮችና ሠራተኞች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ሰምተን ነበር። ጥራቱን ሳይጠብቅ ተጠናቆ በቅርቡ ርክክቡ የተፈፀመው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ ህንፃ ላይ በቅርቡ እምነበረዱን በማንሳት እንደ አዲስ የእድሳት ስራ ማካሄድ ተጀምሯል። በዚህ የክፍለከተማ ህንፃ ውስጥ አንድ አይነስውር ከሰባተኛ ፎቅ ለመውረድ የጠራው አሳንሰር (ሊፍት) ባለመስራቱ ለሊፍቱ በተዘጋጀው ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ ህይወቱ ማለፉን በሚድያ ሲዘገብ መስማታችን ይታወሳል። እኔ እንደምገምተው አንድ ህንፃ ሲ’ሰራ ተቋራጩ የተቀመጠለትን የጥራት ደረጃ በጠበቀ መልኩ መስራቱን የሚቆጣጠር የመንግስት ወኪል ይመደባል። ቢሆንም፣ በተለመደው ‘ግዴለም፣ እንወርዳለን’ በሚል የድርድር ቋንቋ ጥራቱን ሳይጠብቅ የተሰራው ህንፃ ርክክብ በተፈፀመ ማግስት የእድሳት ስራው ይጀመራል። ታዲይ ይኼ የ‘እንወርዳለን’ ድርድር የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በር ጭምር አንኳኩቷል። ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ሬጅስትራር ውስጥ ተመድበው የሚሰሩት ሰራተኞች የተማሪዎችን ውጤት (ግሬድ) ለማስተካከል ገንዘብ እንደሚቀበሉ ከተሰማ ቆይቷል። እንዲህ አይነት የተበላሸ አሰራር የውጤት ግሽበት እንዲከሰት በማድረግ ተማሪዎች የልፋታቸውን ውጤት እንዳያገኙ የሚያደርግ ትውልድ ገዳይ አካሄድ መሆኑን በውል የተገነዘብን አልመሰለኝም።

ታዲያ ምን አለፋችሁ? የማይፈቀደውን ለማስፈቀድ፣ ህጋዊ ያልሆነውን ህጋዊ ለማድረግ፣ ‘እንወርዳለን’ የሚሉት ቋንቋ በየመስሪያ ቤቱ የተለመደ ነገር ይመስላል። እንደዚህ አይነት አነስተኛ ሙስና (Petty corrup­tion) ላይ የሚሳተፉት ቁጥር ስፍር የሌላቸው ወገኖች እጃቸውን ታጥበው ሌሎች ትላልቅ ባለስልጣናት ላይ ጣታቸውን መቀሰራቸው የግብዝነታችንን ጥግ ያሳያል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ በተለምዶ ‘ታሪኬ ባጭሩ’ ተብለው የሚጠሩት ባለሀብቶች በእከክልኝ ልከክልህ ተሞዳሙደው በሚያገኙት ንፋስ አመጣሽ (windfall) ገቢ የኑሮን ዙር በማክረር በደሞዝ የሚተዳደረውን ዜጋ ጤናማ ላልሆነ ቅናት ዳርገውታል። የመንግስት ፕሮጀክቶችና ዕቃ ግዢዎች ከሚልዮን አልፎ በቢልዬን ሲዘረፍ ሲያይ የሚውል የመዝገብ ቤት ሰራተኛ እርሱም ፋይል ከመዝገብ ቤት ላወጣበት ከደሞዙ በተጨማሪ ክፍያ ከደንበኛው እንዲሰጠው ይጠብቃል። የማን ልጅ በልቶ የማን ልጅ ጦሙን ያድራል የሚል ስሜት ይፈጥራል። ሙስና ነውር መሆኑ ቀርቶ ኖርም (አብሮን የሚኖር) ይሆናል። የዘር ማንዘርህን ሕይወት የሚቀይር እስከሆነ ድረስ አምስትና አስር አመትስ ታስረህ ብትወጣ ምን ትሆናለህ ይልሀል። አንዳንዴ መንግስት፣ በራሱ ጊዜ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችል አሰራር ካልዘረጋ፣ ዜጎች በራሳቸው እጅ (ህጋዊ ባልሆነ መንገድ) ሀብት ለማከፋፈል የሚገደዱበት ሁናቴ ይፈጠራል።

የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአንድ ወቅት ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉት ችግሮች መነሻቸዉ በስነ ምግባርና ስነ ዜጋ የታነፀ ትውልድ ባለመፍጠርና ትምህርት ቤቶችና ክበቦች በሚገባ ሃላፊነታቸዉን ባለመወጣታቸው ነዉ ብሎ ነበር። በትምህርት ስርአቱ መሰረት ለተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው የስነ-ምግባርና ስነ-ዜጋ ትምህርት መልካም ዜጋ ከመፍጠር ይልቅ የአጭር ጊዜ የፖለቲካ ጥቅም ማስገኛ መሳሪያ ተደርጎ መወሰዱ ምን አይነት ትውልድ ለመቅረፅ እንዳበቃን ማየት ለሚፈልግ ፍንትው ብሎ የሚታይ እውነታ ነው።

የፀረ ሙስና ማስታወቂያዎቻችን ምድራዊውን ህግ ጨርሰው ከመፅሐፍ ቅዱስና ከቁራን ሰማያዊ ህግ እየጠቀሱ ማስፈራራት የጀመሩበት ሁኔታ ላይ ተደርሷል። የእምነት ተቋማት በህብረተሰቡ ዘንድ የነበራቸው ቀላል የማይባል ተፅእኖ የመፍጠር አቅም በተለይ በከተሞች ኣካባቢ በጊዜ ሂደት እየተሸረሸረ የሄደ ይመስላል። አንዳንድ የቤተ-እምነት መሪዎች ሀይማኖታቸውን የሀብት ማካበቻ መሳሪያ አድርገው ጥቅም ላይ ማዋላቸው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚሉት ሆኖብናል።

ፀረ ሙስና ኮሚሽን ውስጥ የሚሰራ የፀረ ሙስና መኮንን፣ የጀመረውን ክስ ለማቋረጥ ሙስና የሚጠይቅባት የኛው አገር ችግሯ ስር የሰደደ እንደሆነ እንገነዘባለን። አንዳንዴ ሙስናን ለመዋጋት ህግና ፍርድ ቤቶች ጥሩ ማስፈራሪያዎች (deterrent) ቢሆኑም የመጨረሻ መፍትሔ ሊያስገኙልን ግን አይችሉም። “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚል አባባል ያፈለቀ ማሕበረሰብ የመንግስት ስልጣንና ሀላፊነትን የሚያይበት እይታ የተንሸዋረረ ነውና ስር-ነቀል ህክምና ያስፈልገዋል። ዜጎችን፣ በተለይም ህፃናትና ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ፣ ሙስናን የሚጠየፍ አዲስ ትውልድ የመቅረፅ ስራችንን ከወዲሁ ‘ሀ’ ብለን መጀመር ግድ ይለናል። ይኽን ማድረግ ካልቻልን ግን ‘እንወርዳለን’ ብለን እንዳሟረትነው አገሪቱን የማትወጣው አዘቅት ውስጥ ይዘናት እንወርዳለን።

1 Comment

  1. በጥሞና አነበብኩት። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን የሚያህል ትልቅ ተቋም አዲስ ከተፈጠሩ የትምህርት ተቋማት ጋር ዕኩል ለማድረግ ወይም ለማሳነስ የተሰራው ስራ ገና ብዙ ያስከፍለናል። ከደርግ በኋላ የተፈጠረው ትውልድና ትንሽ ከዛም ቀደም ያለው ያደገው በተበላሸ አስተዳደር ውስጥ ነው። ይኽንን ለማስተካከል ሃያ ሰላሳ አመት ይወስዳል። ባልተረጋጋ መንግስት ውስጥ ገና ብዙ የምናጣው ነገር ይኖራል። እያንዳንዱ ዜጋ የሚራመድበት መንገድ፣የተዘጋጁት መናፈሻዎች፣ መኪና የሚነዳበት መንገድ ወዘተ ግብር ከከፈሉ ሰዎች በተሰበሰበ ገንዘብ ነውና ”እኔስ ምን ላዋጣ፣ እኔስ መቼ ነው ግብር ከፍዬ የሌሎችን መዋጮ የምጋራው”ብሎ እስካላሰበ ድረስ ለውጥ በቀላሉ አይመጣም። ቪ8 የተባለ መኪና በመንግስት ሃላፊዎች እጅ እስካለ ድረስ ለውጥ በምንም መንገድ አይመጣም። እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ መንግስትን እነኚህን መኪኖች እንዲያስቆምና የገንዘብ ብክለትን መቆጣጠር እንዲቻል ሁልጊዜ ሳታቋርጡ ካልጮኻችህ ”ከብዬ ነበር”’ የሚተርፍ ምንም አይኖረንም።

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*